ትግራይ፡ በማይካድራ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አብንና የአማራ ብልጽግና ፓርቲዎች ገለጹ

ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለበት ማይካድራ ከሁመራ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ ትገኛለች
የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለበት ማይካድራ ከሁመራ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ ትገኛለች

በሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል ሁመራ አቅራቢያ ማይካድራ ከተማ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ነዋሪዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ሁለት የአማራ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ገዢው የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲና ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ክሰተቱን አስመልከተው ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳሰፈሩት በአካባቢው የነበረው የህወሓት ኃይል በአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ተመትቶ ለመሸሽ በተገደደበት ጊዜ በማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ግድያ ፈጽሟል ብለዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት የሚያስተዳድረው መገናኛ ብዙሃንም በማይካድራ ነዋሪዎች ላይ ግድያ ተፈጽሟል ሲል ዘግቧል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ ሃዱሽ ካሱ የትግራይ ልዩ ኃይል "በምንም ዓይነት ሁኔታ ዘርን መሰረት አድርጎ ጥቃት አይፈጽምም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

"የትግራይ ሕዝብና መንግሥት የዘር ፖለቲካ የሚከተሉ አይደሉም" ያሉት አቶ ሃዱሽ፤ የሚፈጸሙ ሌሎች ድርጊቶችን ለመሸፋፈን የተጠቀመበት ነው ሲሉ ገልፀዋል።

በማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ከአካባቢው ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው አልተሳካለትም።

የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ "ዝርዝሩ በፌደራል መንግሥት በስፋት እንደሚገለፅ ብንጠብቅም፤ ከትህነግ ቡድን ነፃ በወጣችው የማይካድራ ከተማ ነዋሪ በሆኑ የአማራ ወገኖቻችን ላይ ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል" ሲል ገልጿል።

ጨምሮም በዚህ ድርጊት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር በሂደት ተጣርቶ ይፋ የሚደረግ መሆኑን በማመልከት "ግድያው በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን እናምናለን" ብሏል።

ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄም (አብን) ባወጣው መግለጫ ላይ በሽሽት ላይ ያለው ታጣቂ ኃይል "በማይካድራ ከተማና አካባቢው የነበረው የትሕነግ ጦር ከተማዋን ከመልቀቁ በፊት ንፁሀን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ወንጀል እንደፈፀመባቸው" ተመሳሳይ ክስ አቅርቧል።

ንቅናቄው ጨምሮም በጥቃቱ ህፃናትና ሴቶች ሳይቀሩ በአሰቃቂ ሁኔታ በጅምላ መገደላቸውን ገልጿል።

የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ "አሰቃቂ ወንጀል" ያለው ድርጊት የተፈፀመው "በሕዝቦች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ታስቦ መሆኑን" በመጥቀስ፤ የአማራ ሕዝብ "የትግራይን ሕዝብ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ከየትኛውም ጥቃት ጥላ ከለላ ሁነህ ይህን ጊዜ እንድታሳልፈው ይሁን" ሲል አሳስቧል።

በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ ብሎ የሰጋው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግሥት የቅድመ መከላከልና ንፁሀንን የመታደግ ሥራ ላይ ትኩረት እንዲደረግ በአፅንኦት ጠይቋል።

ከዚህ ቀደም በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መፈጸማቸውን መንግሥት መግለጹ የሚታወስ ነው።

አብን አክሎም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚሽን እንዲሰየም አብን በመግለጫው ጠይቋል።

በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል አስተዳደር መካከል ለወራት የዘለቀው ውዝግብ ተካሮ በክልሉ በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸው ይታወሳል።