ትግራይ፡ ግጭቱን ሸሽተው ወደ ሱዳን የገቡ ተፈናቃዮች ከ40 ሺህ ማለፉ ተነገረ

ተፈናቃዮች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

ሦስት ሳምንት ባስቆጠረው የፌደራል መንግሥት ሠራዊትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ከ40 ሺህ በላይ መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ ዩኤንኤችሲአር አስታወቀ።

ኢትዮጵያን በትግራይ ክልል በኩል ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበር የሚገቡ ተፈናቃዮች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ያስታወሰው ድርጅቱ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻም 5 ሺህ ተፈናቃዮች በምሥራቃዊ ሱዳን በኩል እንደገቡም ዩኤንኤችሲአር በድረገፁ ባወጣው መረጃ አስፍሯል።

ዩኤንኤሲአርም ሆነ አጋር ድርጅቶቹ ምግብን ጨምሮ ህይወት አድን እርዳታዎችን እያደረጉ ቢሆንም የተፈናቃዮች ቁጥር በመጨመሩ የሰብዓዊ የእርዳታ የቁሳቁስ ችግርን ጨምሮ ሌሎች እክሎች ገጥሟል ብሏል።

እየጨመረ የመጣውንም ተፈናቃይ ለማስተናገድ በቂ መጠለያም የለም ተብሏል።

በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህፃናት፣ ለነፍሰጡሮችና ለሚያጠቡ 300 የሚሆኑ ተፈናቃዮች የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ ምግብም እየለገሰ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ተጋላጭ የሆኑ ለማኅበረሰብ ክፍሎችም የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም አስታውቋል።

የተፈናቃዮቹን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከድንበር አካባቢ እያራቀ ያለው ድርጅቱ ያለው ቁሳቁስ ውስን መሆን እንዲሁም ወደ ሱዳን መግባት ያለባቸው ርቀት መወሰንም እክል ሆኖብናል ብሏል።

እስካሁን ባለውም በሱዳን ውስጥ 70 ኪሎሜትር ርቀት ባለችው ኡም ራቁባ ግዛት ድረስ ማስፈር መቻሉንም አስታውቋል። ከሰኞ ጀምሮ ባለውም አስከ 8 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች መስፈራቸውም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሰላማዊ ዜጎች ደኅንነት እንዲሁም በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችና የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች እንዳሳሰበውም ዩኤንኤችሲአር አስታውቋል።

ዩኤንኤችሲአርም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት አጋሮች ሁለቱም ወገኖች የዓለም አቀፍ ሕግን አክብረው ንፁሃን ዜጎችን የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ነፃ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና እክል በሌለበት ሁኔታ የሰብዓዊ እርዳታ የሚደርስበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቋል።

በኢትዮጵያ፣ በትግራይ ክልል ያሉ 100 ሺህ ኤርትራውያንም ተፈናቃዮች በግጭቱ ምክንያት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።

ምግብ፣ ውሃ፣ መድኃኒትን የመሳሰሉ መሰረታዊ የሚባሉ አቅርቦቶችን ማድረስ አስቸጋሪ በመሆኑም ለስደተኞቹ ያለው ክምችትም በሳምንት ውስጥ ሊያልቅ መቻሉ ከፍተኛ ስጋት ሆኖብኛል ብሏል ድርጅቱ።

ሁለቱም አካላት ነፃና ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ ዜጎች እርዳታ ወደሚያገኙበት ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸውን እንዲያከብሩ ዩኤንኤችሲአር ጠይቋል።

ድርጅቱ አክሎም ተፈናቃዮች በብሔር ልዩነት ሳይደረግባቸው ደኅንነት ወደሚሰማቸው ቦታ አንዲንቀሳቀሱ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ድንበሮችን እንዲያቋርጡም ሁለቱም ወገኖች ማመቻቸት አለባቸው ብሏል።

በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና ትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል ተቀስቅሶ ለሦስት ሳምንታት በዘለቀው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ እተነገረ ሲሆን፤ ግጭቱን በመሸሽም በአስር ሺዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መግባታቸውን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ገልጸዋል።