ትግራይ፡ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የጠቅላይ ሚንስትሩን የጊዜ ገደብ አንቀበልም አሉ

ደብረፈዒዮን እና ጌታቸው

የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የአገሪቱ ሠራዊት እርምጃ መውሰድ ከመጀመሩ በፊት በ72 ሰዓታት ውስጥ እጃቸውን እንዲሰጡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ጥሪ እንደማይቀበሉት ገለጹ።

የትግራይ ክልል ፕሬዝደንትና የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) እንዲሁም የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባልና ቃል አቀባይ ሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በቴሌቪዥን ቀርበው የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ እንደማይቀበሉና በውጊያው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ መቀለ ከተማ መቃረቡን ተከትሎ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስቀረት የህወሓት አመራሮች እና የትግራይ ክልል ኃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ ባለፈው እሁድ ምሽት የ72 ሰዓታት የጊዜ ገደብ መስጠታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በትግራይ በኩል ላሉ ኃይሎችና ለህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ያስቀመቱት የጊዜ ገደብ ነገ ረቡዕ የሚያበቃ ይሆናል።

ይሁን እንጂ ትናንት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ በጠቅላይ ሚንስትሩ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ እንደማይቀበሉ ገልጸው መታገላቸውን እንደሚቀጥሉ ገልዋል።

በትግራይ መቀመጫውን አድርጎ ነበረው የአገሪቱ ሠሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ በክልሉ ልዩ ኃይል ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ተቀሰቀሰው ግጭት ሦስተኛ ሳምንቱን ሊደፍን ተቃርቧል።

እስካሁን ግጭቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይገደሉ እና ሳይቆስሉ እንደማይቀር ተገምቷል። ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ ግጭቱን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገር ሸሽተዋል።

ደብረጽዮን (ዶ/ር) በትግራይ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ "እኛ ማን እንደሆንን አልተገነዘቡም። መርህ ያለን ሰዎች ነን። ክልላችንን እራሳችን ለማስተዳደር መስዋትነት እንከፍላለን" ብለዋል።

ጨምረውም የተለያዩ የትግራይ ከተሞች በአገር መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር መውደቃቸውን አረጋግጠው፤ "የፌደራሉ መንግሥት እንደሚለው ግን በህወሓት ኃይል ላይ ሽንፈት እየደረሰ አይደለም" ብለዋል።

ይልቁንም የህወሓት ኃይል በፌደራል ኃይሎች ላይ ድል እየቀዳጀ ነው ብለዋል። ይህ ግን እስካሁን በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያስቀመጡትን "ቀነ ቀጠሮ" እንደማይቀበሉ ጠቅሰው የትግራይ ኃይል በትግሉ እንደሚቀጥል ትናንት ገልጸዋል።

"እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ ጠመንጅ የያዘም ያልያዘም . . . የሚመክተው ጦርነት ነው" በማለት ሕዝቡ ባለው መሳሪያ እንሚዋጋ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ መቀለ መቃረቡን ተከትሎ በሚቀጥሉት ቀናት በሚደረጉ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለከተማዋ ነዋሪዎች ደኅንነት ጥንቃቄ እንዲደረግ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የተባበሩት መንግሥታት ጠይቀዋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል በሁለቱም ወገን ያሉ የጦር አዛዦች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕጎችና መርሆችን እንዲያከብሩ ጠይቋል።

መገናኛ ብዙሃን የአክሱም የአየር ማረፊያው አውሮፕላን መንደርደሪያ ተቆፋፍሮ እና ህንጻው ወድሞ አስይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, FANA

የምስሉ መግለጫ, መገናኛ ብዙሃን የአክሱም የአየር ማረፊያው አውሮፕላን መንደርደሪያ ተቆፋፍሮ እና ህንጻው ወድሞ አስይተዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ

ባለፈው ሳምንት የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በትግራይ ክልል የሚገኙ ቁልፍ ከተሞችን መቆታጠሩ የተነገረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሽረ፣ አክሱም፣ አደዋና አዲግራት ይገኙባቸዋል።

መንግሥት እነዚህን ከተሞች መቆጣተሩን ተከትሎ እንዳለው የህወሓት ኃይል እንዲለቅ የተደረገባቸው ከተሞች ውስጥ የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን እያወደሙ እየሸሹ ነው ሲል ከሷል።

በተቋማት፣ በመንገዶችና በድልድዮች ላይ ጉዳት ደርሰወል የተባለ ሲሆን የፌደራሉ መንግሥት መገናኛ ብዙሃን በአክሱም አየር ማረፊያ የደረሰውን ጉዳት አቅርበዋል። በዚህም የተቆፋፈረ የአየር ማረፊያው አውሮፕላን መንደርደሪያ እና ጉዳት የደረሰበት የአየር ማረፊያው ሕንጻን ታይቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ከአክሱም አየር ማረፊያ በተጨማሪ ከስድስት ያላነሱ ድልድዮች እንዲፈርሱ መደረጋቸውን እና መንገዶች መቆፈራቸውን ተናግረዋል።

ምንም እንኳ በጉዳዩ ላይ የህወሓት አመራሮች አስተያየታቸውን ባይሰጡም፤ ደብረጽዮን (ዶ/ር) ባሳለፍነው እሁድ ለሬውተርስ የትግራይ ኃይሎች የፌደራል መንግሥት ሠራዊትን የሚያደርገውን ግስጋሴ ማዘግየት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ትግራይ

ዲፕሎማሲያዊ ጥረት?

የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት አሳስቦኛል ብላለች። አረብ ኢሚሬትስ በጉዳዩ ላይ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ግነኙነት በማድረግ ለጉዳዩ መፍትሄ እያፈላለገች መሆኑን አስታውቃለች።

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሳ ግጭቱን ለማስቆም ሦስት የቀድሞ ፕሬዝደንቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ አርብ ዕለት ገልጸው ነበር።

አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን ጠቅላይ ሚንስትሩ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለአፍሪካ መሪዎች ካለ አክብሮት የመነጨ ይህን ልዑክ ተቀብለው እንደሚያነጋግሩ አስታውሰው፤ "ከህወሓት ኃይሎች ጋር ግን እንደ ሕጋዊ አካል ቆጥሮ የሚደረግ ውይይት አይኖርም" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ማሞ ምህረቱም ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ "ከወንጀለኞች ጋር አንመካከረም . . . ለፍትሕ እናቀርባቸዋለን። በጠረጴዛ ዙሪያ ከእነርሱ ጋር አንደራደርም" ብለው ነበር።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባትና መካሰስ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ግጭት ማምራቱ ይታወሳል።

ባለፉት ሳምንታት በተካሄዱት ወታደራዊ ዘመቻዎች የመንግሥት ኃይሎች የተለያዩ ከተሞችን መያዛቸው የተነገረ ሲሆን በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ አቅራቢያ መድረሳቸውም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ መቀለ የአገሪቱ ሠራዊት ከመንቀሳቀሱ በፊት ሊደርስ ይችላል የተባለ ጉዳትን ለማስቀረት የትግራይ ክልል ኃይሎችን የህወሓት አመራሮች እጃቸውን እንዲሰጡ ነገ ረቡዕ የሚያበቃ የ72 ሰዓታት የጊዜ ገደብ አስቀምጠዋል።