ትግራይ፡ አምነስቲና የተባበሩት መንግሥታት ለመቀለ ሰላማዊ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲደረግ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ መቀለ በተቃረበበት ጊዜ በሚቀጥሉት ቀናት በሚደረጉ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ወቅት ለከተማዋ ነዋሪዎች ደኅንነት ጥንቃቄ እንዲደረግ ተጠየቀ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ለህወሓት አመራሮች እና ተፋላሚዎች የ72 ሰዓታት የመጨረሻ ጊዜ ገደብ መስጠታቸውን ተከትሎ በመቀለ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ሊደርስ የሚችለው አደጋ እንዳሳሰባቸው የተበባሩት መንግሥታት እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቀዋል።
ሦስት ሳምንት ለመድፈን በተቃረበው ግጭት የፌዴራሉ መንግሥት አሁን በትግራይ ዋና ዋና የሚባሉ ከተሞችን መቆጣጠሩን እና ወደ ክልሉ መዲና መቃረቡን አስታውቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንም ትናንት በነበራቸው መግለጫ መቀሌ በመከላከያ ሠራዊት ከ50-60 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ተከባ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለህወሓት መሪዎች በሰጡት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በንሑሃን እና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከዚህ በኋላ ብቸኛው አማራጭ እጅ መስጠት መሆኑን አስገንዝበው ነበር።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚገመቱ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች አስፈላጊው ከለላና ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
በተመሳሳይ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ሁለቱ ኃይሎች ለሰላማዊ ዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቋል።
በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ የሚደርስበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹም አስገንዝቧል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮስ ሙቼና፤ "በሁለቱም ወገን ያሉ የጦር አዛዦች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕጎችና መርሆችን እንዲያከብሩ እጠይቃለሁ። በሰላማዊ ሰዎችና ወታደራዊ ባልሆኑ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚቻለውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርጉ፤ ሰላማዊ ሕዝብ በሚበዛባቸው ሰፈሮች የወታደራዊ ቁሳቁሶች ክምችትን እንዲያስወግዱ፣ የወታደሮች እንቅስቃሴም በሰላማዊ ነዋሪዎች መኖርያ አካባቢ እንዳይሆን ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።
በተጨማሪም ተዋጊዎች ሰላማዊ ዜጎችን ጋሻ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አምነስቲ ጠይቋል።
ከመቀለ ከተማ ባሻገርም በመላው ትግራይ ክልል ለደረሰው ሰብአዊ ቀውስ እርዳታ እንዲደርስ ለማስቻል ተራድኦ ድርጅቶች እንደልብ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ለማገዝ ዕድሉን እንዲመቻች፣ የግንኙነቶች መስመሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ የስልክና የኢንተርኔት ግንኙነቶች ክፍት እንዲደረጉ አምነስቲ አሳስቧል።
አስተማማኝ መረጃ መግኘት አስቸጋሪ በሆነበት በትግራይ እየተካሄደ ባለው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ሳያጡ እንደማይቀር የእርዳታ ድርጅቶች ይገምታሉ።
በተጨማሪም ከ30ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችም ግችቱን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን እንደተሰደዱ እተነገረ ነው።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባትና መካሰስ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።
በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ግጭት አምርቶ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የአገሪቱ ሠራዊት ወደ ክልሉ ዋና ከተማ መቃረቡ ተነግሯል።














