በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት ዐቢይ አሕመድ ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, HOPR
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በተመሰረተው ምክር ቤት አማካይነት ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን እንዲመሩ ተሰይመዋል።
አገሪቱ ውስጥ ተከሰተን ፖለቲካዊ ቀውስን ተከትሎ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነበር ዐቢይ አሕህመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ኃላፊነት ተረከቡት።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ዐቢይ አሁን ለሙሉ የሥልጣን ዘመን ኃላፊነቱን ትተረክበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማን ናቸው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን የመጡት ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያ ወደ የእርስ በእርስ ግጭት ለመግባት ከጫ ደርሳለች ተብሎ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን እንደተረከቡ ታሪካዊ የሚባሉ የለውጥ እርምጃዎችን ወስደዋል፤ አንዳንዶቹ ለውጦችም በኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ ነበሩ።
ኢትዮጵያ ዘወትር ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻናት እንዳይገልጹ ታደርጋለች፣ ተቃዋሚዎች የሚታሰሩባት እና ለተቃውሞ አደባባይ በሚወጡ ዜጎች ላይ የማያዳግም እርምጃ የምትወስድ አገር ናት እየተባለች በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ የምትተች አገር ነበረች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ግን ይህ ሁሉ ተቀየረ። ከኤርትራ ጋራም ሰላም ወረደ። ለዚህ ጥረታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2019 የሰላም ኖቤል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእርሳቸው በፊት ሥልጣን ላይ ከነበሩት እና "ጠላት" ከሚባሉት ጋር ለመገናኘት እንዲሁም ስላም ለማውረድ ቁርጠኛ መሆናቸው ተስተውሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አባት ሐምሌ 2011 ላይ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ "ከሁሉም ጋር ጓደኛ የሆነ ልጅ ነው" ሲሉ ልጃቸውን ገልጸው ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ማን ናቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኙ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ያመጣቸው ለሦስት ዓመታት የዘለቀው ተቃውሞ በኦሮሚያ ውስጥ መሠረት ያደረገ ነበር። ለዓመታት በዘለቀው ታውሞ በርካቶች ተገድለዋል በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል።
ተቃዋሚዎች ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እና ዋነኛው የኦሮሞ ሕዝብ የኢትዮጵያ ትልቁ ብሔር ሆኖ ሳለ ሕዝቡ ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለዓመታት ተገሎ ቆይቷል የሚል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ወደ ስልጣን ሲመጡ ይህ መቀየር ጀመረ።
ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አካል የሆነው የኦሮሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢህዴድ) ሊቀመንበር ተደርገው ተሹመው ነበር።
ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሦስት አስርት ዓመታት ገደማ የኢትዮጵያ ፖለቲካን ተቆጣጥሮ የቆየውን ኢሕአዴግ በማክሰም ብልጽግና የተሰኘና ከቀድሞው ገዢ ፓርቲ ሰፋ ያለ መሰረት ያለውን ፓርቲ መስርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት በኢሕአዴግ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ሆኖ የቆየው ህወሓት ብልጽግና ፓርቲን ለመቀላቀል አልፈለገም።
የ44 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ክርስቲያን እና ሙስሊም ከሆኑ ወላጆች የተገኙ ሲሆን የተወለዱት ደግሞ በአሉአባቦራ ኦሮሚያ ነው።
ዐቢይ አሕመድ በውትድርና ሕይወታቸው አስከ ሌፍተናንት ኮሎኔል ማዕረግ ለመድረስ ችለዋል። ከዚያም የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የተባለው ተቋምን መስርተው ይመሩም ነበር።
በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርግ በነበረው መንግሥት ውስጥ፤ ይህ ተቋም በአገሪቱ የሚደፈጸሙ የሳይብር - ሴኩሪቲ ጥቃቶችን መከላከል ዋና ዓላማው ነበር።
በተከታይነት ደግሞ ዐቢይ የአገሪቱ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙም በኋላ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሚገኘው የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ሌሌች እንዲሰማሩ በመፍቀድ ዘርፉን ለማዘመን ቃል ገብተዋል።
ቁልፍ እውነታዎች፡ ዐቢይ አሕመድ
ኦሮሞ ከሆኑት ሙስሊም አባላታቸው እና አማራ ከሆኑት ክርስቲያን እናታቸው በአጋሮ ከተማ ተወለዱ። ዐቢይ ገና በአስራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ እያሉ ደርግን መታገል ጀምሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰላም እና ደኅንነት ጥናት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል። የማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ 'በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ' ከለንደኑ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ግሪንዊች አግኝተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን ይናገራሉ።
እአአ 1995 ላይ በሩዋንዳ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባል ሆነ አገልግለዋል።
1999 ላይ የኢትዮጵያን የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲን አቋቁመዋል። የኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቦርድ አባል ሆነውም አገልገለዋል።
2002 ላይ የኦሮሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅትን (ኦህዴድ) በአባልነት ተቀላቅለው 2007 ላይ የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል መሆን ችለዋል።
2008 ላይ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
2010 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።
2011 ላይ ኢሕአዲግ አንዲከስም ተደርጎ የልጽግና ፓርቲን መሠረቱ።
2012 ላይ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ሰላም እንዲሰፍን ላደረጉት ጥረት የኖቤል የሰላም ሽልማትን ተሸለሙ።
2013 ላይ በትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ መገደዳቸውን አስታወቁ።
የኖቤል የሰላም ሽልማት
ጠቅላይ ሚንሰትር ዐቢይ ከኤርትራ ጋር የደረሱት የሰላም ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነትም ሰላምም የሌለበት ሁኔታን የቀየረ ነበር።
ይህ ተግባራቸውም የ100ኛው የኖቤል ሽልማት አሸናፊ እንዲሆኑ አደርጓቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦስሎ የኖቤል ሽልማታቸውን ሲቀበሉ የሚከተውን ንግግር አድርገው ነበር።
"ጦርነት ለመቀስቀስ የሚያስፈልገው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነው። ሰላም ለመገንባት ግን መንድር እና ሕዝብ ያስፈልጋል።
"ለእኔ ሰላምን መንከባከብ ማለት ዛፍ እንደመትከል እና ማሳደግ ነው። ዛፎች ለማደግ ጥሩ አፍር እና ውሃ እንደሚፈልጉት ሁሉ፤ ሰላምም ያልተቋረጠ ትጋት፣ ያልተቆጠበ ትዕግስት እና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል።"
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማታቸውን ከተረከቡ በኋላ በአገሪቱ የተከሰተውን "ሞት እና መፈናቀል" ምክንያት በማድረግ የኖቤል ኮሚቴው የሰጠውን ሽልማት እንዲሰርዝ ጥያቄ ያቀረቡ ነበሩ።
ይህን ተከትሎም የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴው መግለጫ ለማውጣት ተገዶ ነበር። ኮሚቴው በመግለጫው ለጠቅላይ ሚንስትሩ የኖቤል ሽልማት መስጠቱ ትክክል አልነበረም ብሎ እንደማያስብ አስታውቋል።
መደመር
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ 'መደመር' የሚለው ቃል በበርካቶች ዘንድ ጥቅም ላይ ሲውል የቆየ ቃል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት የሚያስችል አካሄድ እንደሆነ ይናገራሉ።
መደመር የተሰኘው የጠቅላይ ሚንስትሩ መጽሐፍም በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ከታተመ በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ኮፒ መሸጡ ተነግሯል።
280 ገጽ እና 16 ምዕራፎች ያሉት መጽሐፉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፍልስፍና ያትታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዘር የተከፋፈለችው ኢትዮጵያን በአንድነት ስሜት እንድትቆም ይሻሉ፤ በተመሳሳይ ብዝሃነት እንዲከበር ይሻሉ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ፍልስፍና የተለያዩ ወይም የሚቃረኑ ሃሳቦችን አንድ ላይ በማምጣት መግባባት ላይ መድረስ ይቻላል የሚል መሠረት አለው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እአአ 2017 ላይ በደኢህዴን ስበሰባ ላይ "አንድ አማራጭ ነው ያለን። ይህም አንድ መሆን ነው፤ መተባበር እና እርስ በእርስ መተጋገዝ ብቻ ሳይሆን መኖር እንዲቻለን አንድ መሆን አለብን። ሌላኛው አማራጭ መገዳደል ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ቀውስ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ መገደዳቸውን ያስታወቁት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ላይ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከዚህ ውሳኔ እንዲደርሱ ያደረገው ምክንያት የህወሓት ኃይሎች የአገር መከላከያ ሠራዊት አንድ አካል በሆነው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ መሆኑን ተናግረዋል።
"ስለዚህ የፌደራሉ መንግሥት ወታደራሚ አማራጭ እንዲወስድ ተገዷል" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር እና በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ከለውጡ በኋላ ለርካታ ወራት ቆይቷል።
የስልጣን ሽኩቻ፣ ምርጫ እና የተወሰዱ ፖለቲካዊ የለውጥ እርምጃዎች በሁለቱ ወገን መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ለሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ህወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ ኃይል ሆኖ ቆይቷል። የህወሓት አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግን ከስልጣን ተገፍተናል ሲሉ ይከሳሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥና ማሻሻያዎችን ሲያደርጉ የህወሓት ኃይሎች ግን ደስተኛ አልነበሩም፤ ይህም ፖለቲካዊ ቀውስ አስከተለ።
የህወሓት አመራሮች የጠቅላይ ሚንስትሩን ፈጣን የለውጥ እርምጃ ስልጣንን ለማማከል የሚደረግ ጥረት እንደሆነ እና የኢትዮጵያን የፌደራል ሥርዓት ለማፍረስ የሚደረግ ጥረት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።
ቀጠናዊ ተጽእኖ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር የሥልጣን ዘመናቸውን አለመግባባት በተፈጠረባቸው ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በማሸማገል ተልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በሱዳን ከአል-በሽር መወገድ በኋላ የአገሪቱ ሠራዊትና ተቃዋሚዎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ይህም ድርድር በሱዳን ሠራዊቱና እና ሲቪሎች ሥልጣን ተጋርተው አገሪቷ በሽግግር መንግሥት እንድትመራ አስችሏል።
ጂቡቲ እና ኤርትራም ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነታቸውን እንዲሰያሻሽሉ ጥረት አድርገዋል።
ሶማሊያ እና ኬንያም በሚጋጩበት የባሕር ጠረፍ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱን አገራት አሸማግለዋል።
ይህን ብቻም ሳይሆን የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና የአማጺያኑ መሪ ሬክ ማቻር ከስምምነት እንዲደርሱ የተቻላቸውን አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ እየተወሰደ ያለውን ወታደራዊ እርምጃ "ሕግ የማስከበር እርምጃ ነው" ቢሉትም ከሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ከእርዳታ አቅርቦት አንጻር ምዕራባውያንና ዓለም አቀፍ ተቋማት በመንግሥታቸው ላይ ተለያዩ ግፊት እያደረጉ ነው።
ቢሆንም ግን መንግሥታቸው ከአማጺያኑ ጋር ድርድር እንደማይደረግ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ በተደጋጋሚ አሳስበዋል።












