ትግራይ ፡ ህወሓት ወደ ሽምቅ ተዋጊነቱ ይመለስ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ለሦስት አሥርታት ለሚጠጋ ጊዜ በተደላደለ ሥልጣን ላይ የነበረው ህወሓት በትግራይ ክልል ገዢ ሆኖ ሲኖር በዚያ ሁሉ የጊዜ ርዝማኔ ይህ ነው የሚባል ተቀናቃኝ አጋጥሞት አያውቅም።
ከክልሉ አልፎም በመላው ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ስንክሳር ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ቆይቷል። አሁን ግን ይህ እድሜ ጠገብ ፓርቲ ዳግም ወደ በረሀ ሊመለስ ይመስላል። በእርግጥ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ለዚህን ያህል ጊዜ ተጽእኖ ፈጣሪ የነበረው ፓርቲ ወደ ሽምቅ ውጊያ ይመለስ ይሆን?
ዳግም ወደ በረሃ?
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይህ እንዳይሆን ነው ፍላጎቱ።
በጥቅምት 23/2013 ዓ.ም የተጀመረው የማጥቃት እርምጃ ምናልባትም የህወሓት ግብአተ መሬትን የሚፈጽም ሊሆን ይችላል።
በመከላከያ የሚወሰደው እርምጃ የፓርቲውን 70 የሚሆኑ አመራሮችና ወታደራዊ መኮንኖችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚደረግ "ሕግን የማስከበር" ዘመቻ እንደሆነ መንግሥት እገለጸ ነው።
ከእነዚህ ማዘዣ ከወጣባቸው ግለሰቦችና ወታደራዊ መኮንኖች መካከል 17 ዓመታት ሙሉ ትጥቅ ትግል አድርገው በ1983 ዓ.ም አዲስ አበባን የተቆጣጠሩ የፓርቲው 'አባቶች' ይገኙበታል።
ያን ሁሉ ዘመን የትጥቅ ትግል መርቶ አገሪቱን የተቆጣጠረው የህወሓት ታጣቂ ቡድን ከድል በኋላ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የአገሪቱን ወታደራዊና የደኅንነት መዋቅር ተቆጣጥሮ ቆይቷል። የዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት ግን ይህን ሁኔታ ከሥር መሠረቱ ለውጦታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ህወሓት መራሹ ሥርዓት ለሦስት አሥርታት ያህል ጨቋኝና በሙስና የተጨማለቀ ሆኖ እንደቆየ መናገር ጀመሩ። ይህንን ክስ ህወሓት አይቀበለውም።
የጠ/ሚኒስትር ዐብይ መምጣትን ተከትሎ የለውጥ ኃይሉ የአገሪቱን ደኅንነት መዋቅር ቀስ በቀስ ከህወሓት መዳፍ ፈልቅቆ በእጁ ማስገባት ቻለ።
በተመሳሳይ ህወሓትና ማዕከላዊ አመራሩ ወደ ትግራይ ክልል እያፈገፈገ ነበር። በማዕከላዊ መንግሥቱና በህወሓት መሀል የነበረው መቃቃር እየሰፋ መጣ።
ከዚህ በኋላ የመጣው ሁነኛ ክስተት ከሳምንታት በፊት ህወሓት በክልሉ የሚኘውን የሰሜን ዕዝን አጥቅቶ መቆጣጠሩ ነበር።
"ለመሞት ዝግጁ ነን"
ግጭቶችን ቀድሞ በመተንበይና በመተንተን የሚታወቀው መንግሥታዊ ያልሆነው የዓለም አቀፉ ቀውስ አጥኚ ቡድን (በምህጻሩ ICG) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝን "የፌዴራል መንግሥቱ ጠንካራው ዕዝ" ሲል ይገልጸዋል።
ህወሓት ሰሜን ዕዝን ከቆጣጠረ በኋላ ሮኬቶችና ሚሳኢሎችን በእጁ ማስገባት ችሏል። ይሁንና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአየር ኃይሉ ያይላል። ተዋጊ ጄቶችና የጦር ሄሊኮፕተሮች በእጁ ያስገባ ጠንካራ መከላከያ ጦር ነው።
ህወሓት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ የተሰማው ማዕከላዊው መንግሥት በክልሉ በተናጠል ከተካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ በመስተዳደሩ ላይ በጀት ዕቀባ ካደረገ በኋላ ነበር።
ቀደም ሲል በትግራይ የፌዴራል መንግሥቱ ሕገ ወጥ ያለው ምርጫ ተካሂዶ ነበር። በዚህም በፌደራል መንግሥቱ ና በትግራይ ክልል መካከል አለመግባባቱ እየሰፋ መጥቶ ነበር።
የፌዴራል መንግሥት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን አራዝሞ እያለ ትግራይ ተነጥላ ምርጫ ማካሄዷ ማዕከላዊ መንግሥቱን ደስተኛ አላደረገውም። የሕግ መተላለፍ ነውም ብሏል።
የህወሓት ባለሥልጣናት በበኩላቸው የሰሜን ዕዝን የተቆጣጠርነው የፌዴራል መንግሥት ወደ ክልላችን መጥቶ ወረራ መፈጸሙ አይቀሬ እንደሆነ በመረዳታችን ነው ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በበኩላቸው በሰሜን ዕዝ ላይ ህወሓት የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ አሁን "ቀዩ መስመር ታለፈ" ብለዋል። ወታደራዊ እርምጃም በአስቸኳይ እንዲጀመርም አዘዋል።
መንግሥት በህወሓት አመራሮችና በክልሉ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ 22ኛ ቀን ሆኗል።
ከትናንት [ሐመስ] ጀምሮ ሠራዊቱ የመጨራሻውን ሦስተኛ ምዕራፍ እርምጃ እንዲወስድም ታዟል። ይህ ወታደራዊ ኦፕሬሽን የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ገብቶ የህወሓትን ከፍተኛ አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋልን ግብ ያደረገ ነው።
ይህ ወታደራዊ ኦፕሬሽን በሚቀጥሉት ቀናት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ማዕከላዊው መንግሥት ያምናል።
ነገር ግን የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ይህ በቀናት የሚገባደድ ነው የተባለው ጥቃት የተዋጠላቸው አይመስልም።
ለዜና ወኪሉ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት "እኛ የመርህ ሰዎች ነን። ክልላችንን የማስተዳደር መብታችንን ለማስጠበቅ ስንል ለመሞትም ቢሆን ዝግጁ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሠራዊት ብልጫ
የዓለም አቀፉ የግጭቶች ምርምር ቡድን ባልደረባና የኢትዮጵያ አጥኚ የሆኑት ዊሊያም ዴቪሰን እንደሚሉት ህወሓት ከ200 ሺህ ባላይ ተዋጊ ሠራዊት ማሰባሰብ ችሏል። ይህም በየአካባቢውና ገጠሩ የሚገኙ ሚሊሻዎችን እና የልዩ ኃይል አባላትን የደመረ አሐዝ ነው።
"ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፖለቲካ ምኅዳሩ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ በትግራይ ክልል መጠነ ሰፊ የወታደር ምልመላና ስልጠና ሲደረግ ነበር" ሲሉ አጥኚው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ በምህጻሩ አይሲጂ ተብሎ የሚጠራው የግጭቶች አጥኚ ቡድን የኢትዮጵያን ሠራዊት ግዝፈት በቁጥር ሊገምት አልፈቀደም።
ነገር ግን ሮይተርስ ዜና አገልግሎት አንድ ጄንስ የሚባል የደኅንነት አሐዝ መረጃ ሰብሳቢ ቡድንን ዋቢ አድርጎ እንደጠቀሰው መከላከያ ሠራዊቱ 140 ሺህ የሚሆን የታጠቁ፣ የበቁና የነቁ ወታደሮች አሉት ይላል።
ይህ ግምታዊ አሐዝ እውነትነት ካለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁጥር ከህወሓት የወታደሮች ቁጥር ያነሰ ነው ማለት ነው።
ነገር ግን መዘንጋት የሌለበት አሐዙ ትክክል ነው ቢባል እንኳ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከየክልሎቹ የተውጣጡ የልዩ ኃይል አባላትን ማካተቱ ቁጥሩን ያመጣጥነዋል።
የኢትዮጵያ ሕግ ክልሎች በክልላቸው ያለውን ሰላም ለማስጠበቅ ኃይል እንዲኖራቸው የሚፈቅድ ነው።
ከልዩ ኃይሎች ውስጥ በተለይም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በወታደራዊ ጥቃቱ መጀመርያ አካባቢ በምዕራብ ትግራይ በኩል መከላከያ ሠራዊት ቁልፍ ቦታዎችን እንዲቆጣጠር አግዞታል።
አማራ ክልል በዚሁ አካባቢ ከሚዋሰነው የትግራይ ክልል ጋር የግዛት የይገባኛል ጥያቄዎች እንዳሉት ይታወቃል።
"በምዕራብ ግንባር የአማራ ልዩ ኃይልና የፌዴራሉ መከላከያ ሠራዊት ጥምረት የትግራይ ኃይል ላይ ከፍተኛ ብልጫ ስለሚኖረው ቁጥጥሩ ጠንካራ እንደሚሆን ይገመታል" ይላሉ ሚስተር ዴቪሰን።
"ሌላው ነጥብ በምዕራቡ የትግራይ ክፍል ሜዳማ የሆነ መሬቶች ስለሚበዙ መደበኛ ውጊያ (conventional army) ለሚያደርገው ማዕከላዊው መንግሥት የተመቸ ዕድል ሰጥቶታል" ይላሉ ባለሞያው።
ባለሙያው ይህን የሚያነሱት ሠራዊቱ ወደ ማዕከላዊ ትግራይ በተጠጋ ቁጥር እንዲሁም ወደ ምሥራቅ ትግራይ መቀለ በቀረበ ቁጥር የመልከዓ ምድሩ ተራራማ እየሆነ እንደሚሄድ ለመጠቆም ነው።
እንዲህ ዓይነቱ ድንጋያማ፣ ደረቅና ተራራማ መልከአምድር ደግሞ ለሽምቅ ውጊያ እንጂ ለመደበኛ ውጊያ የሚመች አይሆንም።
የትግራይ በሮች መዘጋት
አቶ አርሄ ሐመድናካ ከቀድሞው የደርግ መንግሥት በተቃራኒ ሆነው በሽምቅ ውጊያ የተሳተፉ ሰው ናቸው። አሁን በስዊድን የሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባል ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት የመከላከያ ሠራዊት በምዕራብ በኩል የከፈተው ጥቃት በዋናነት ከሱዳን ጋር ያለውን ድንበር ለመቆጣጠር ያለመ ነበር።
ይህ እጅግ ቁልፍ እርምጃ እንደሆነ አቶ አርሄ ይገልጻሉ። ይህ መሆኑ ህወሓት ከ29 ዓመት በፊት በዚያ አካባቢ ጦር ቀጠና አቋቁሞ እንደነበረው ሁሉ አሁን ያን እንዳያደርግ ከልክሎታል ይላሉ።
"ለህወሓት ብቸኛው መተንፈሻ፣ ለማምለጥ መውጫ ቀዳዳ፣ እንዲሁም መሳርያ ለማስገባት ያለው ዕድል የሱዳን ድንበር ነበር" ሲሉ የቦታውን ወሳኝነት አስረግጠው ይናገራሉ።
ከዚህ ሌላ ህወሓት በደርግ ጊዜ ከሻዕቢያ ጋር ተቆራኝቶ ግዙፉን የደርግ ሠራዊትን ሲታገል የቀይ ባሕር መተለለፊያ ነበረው። አሁን ግን ያ የለም።
ይህም የሆነበት ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ሁነኛ ወዳጅ በመሆናቸው ነው።
ህወሓት መላ አገሪቱን በሚቆጣጠርባቸው ዓመታት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከኢትዮጵያ ጋር መራር ውጊያ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
"ጊዜው ተቀየረ። ህወሓት በየት በኩል መተንፈሻ ይኖረዋል። በሰሜን በኩል ያሉት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው። ለዚያውም የህወሓት ዋንኛ ጠላት" ይላሉ የቢቢሲው የትግርኛ ቋንቋ ኤዲተር አቶ ሳሙኤል ገብረሕይወት።

ህወሓት መጪው እጣ ፈንታው ምንድነው?
ቢቢሲ ከኤርትራ ያገኛቸው ምንጮች እንደሚያመላክቱት የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ኤርትራ በድንበር በኩል ዘልቀው እንደሚገቡ ጠቋሚ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት በጦርነቱ መሀል ማፈግፈግ ሲኖርባቸው ወደ ኤርትራ ያፈገፍጋሉ። መልሶ ራሳቸውን ለማደራጀት ሲሹም ይህንኑ ያደርጋሉ። የቆሰሉ አባሎቻቸውን ለማከምም የወታደራዊ ሆስፒታሎች ይገባሉ።
ይህ የኤርትራ ምንጮች ለቢቢሲ ያቀበሉት መረጃ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በኤትራ መንግሥት ተቀባይነት አላገኘም።
የኤትርራ መንግሥት በዚህ ጦርነት እጄን አላስገባሁም ይላል፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም በዚህ ይስማማል።
"ትግራይ ታጥራለች። የህወሓት ሠራዊት ከዚህ በኋላ መደበኛ ጦርነትን ሊቋቋም አይችልም" ይላሉ የአይሲጂ ተመራማሪው ሚስተር ዴቪሰን።
ነገር ግን ይህ ማለት የማዕከላዊው መንግሥት በአንድ ጀንበር ድል ያደርጋል ማለት አይደለም።
አቶ አርሄ በጦርነት ታሪክ ሽምቅ ውጊያ ተዋጊዎች በሠራዊት አደረጃጀትና በትጥቅ በአያሌው የሚልቋቸውን ኃይሎች መቋቋም የቻሉበት በርካታ አጋጣሚ ይጠቅሳሉ።
"አሜሪካ ያ ሁሉ ውስብስብ ሰው አልባ ተዋጊ ጄትና የጦር መሣሪያ የበላይነት እያላት ታሊባን አልተደመሰሰም" ይላሉ። በተመሳሳይ "የሁቲ ሚሊሻዎች በየመን የኢምሬቶችና የሳዑዲን የመሣሪያ የበላይነትን ተቋቁሞ አለ።"
ሚስተር ዴቪድሰን እንደሚሉት መከላከያ ሠራዊቱ ወደ መቀለ በሚገሰግስበት በዚህ ወቅት የትኞቹን ከተሞች እንደተቆጣጠሩ፣ የትኞቹን አልፈው እንደመጡ የተብራራ መረጃ የለም።
ያም ሆነ ይህ በርካታ የትግራይ ተዋጊዎች ወደ አቅራቢያ ተራሮችና መንደሮች ማፈግፈጋቸው አይቀርም። ይህም ለሽምቅ ውጊያ ራሳቸውን ለማዘጋጀት የሚያደርጉት ጥረት ነው የሚሆነው።
"የፌዴራል ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሳይሆን ብዙ የትግራይ ተወላጆች ጣልቃ ገብነቱን ይቃወሙታል። የሚቃወሙትም ይህ ጣልቃ ገብነት በሕጋዊ መንገድ የተመረጠን አስተዳደር ለማስወገድ የሚደረገው አድርገው ስለሚወስዱት ነው።"
ከዚህም ባሻገር በርካቶች የክልሉ ተወላጆች ህወሓት በ1983 አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ያመጣውን የፌዴራል ሥርዓተ-አስተዳደር ይደግፉታል። ይህ ዓይነቱ አስተዳደር የፖለቲካ፣ የቋንቋና የባሕል ነጻነታቸውን የሚያስጠብቅላቸውና የተሻለው ሥርዓት እንደሆነም በስፋት ያምናሉ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ህወሓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሐዳዊ ሥርዓት ሊያሰፍኑ ነው የሚሞክሩት ስትል ትከሳለች።
የቢቢሲው ትግርኛ ኤዲትር አቶ ሳሙኤል እንደሚሉት ከሆነ ግን አሁን ባለው ሁኔታ "ምንም እንኳ የትግራይ ብሔርተኝነት መፋፋም ለህወሓት ድጋፍ የሚያስገኝለት መልካም ዜና ቢሆንም፤ ከዚህ ተነስተን በርካቶች (ከህወሓት ይልቅ) የፌዴራል መንግሥትን ሊደግፉ አይችሉም ብለን ልንደመድም አንችልም" ይላሉ።
ደርግን በመጣሉ የትጥቅ ትግል ወቅት የትግራይ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ከህወሓት ጋር ይወግን ነበር። ነገር ግን ህወሓት ሦስት አሥርታት ለሚጠጋ ጊዜ በሥልጣን ከቆየ በኋላ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ሥርዓቱ ያመጣው ጭቆናናበሙስና መንሰራፋቱ ድጋፋቸው እንዲሸረሸር አድርጎታል።
አቶ ሳሙኤል እንደሚያምኑት የመቀለ ጦርነት መጨረሻ የህወሓትን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል። ምናልባትም ህወሓት ሽምቅ ውጊያ እንዲጀምር የሚያደርገው ሊሆንም ይችላል።
ይሁንና አቶ ሳሙኤል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የበላይነት ቢይዝም እንኳ በሁሉም ወገኖች ዘንድ የፖለቲካ ንግግር ሳይኖር ህወሓትን በማሸነፍ ብቻ በክልሉ ግጭትን እስከናካቴው ማጥፋት ይቻላል የሚባለው ሐሳብ አይታያቸውም።













