ትግራይ ፡ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኞች አዲስ አበባ ገቡ

ከግራ ወደ ቀኝ፤ የቀድሞውን የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዮአኪም ቺሳኖ፣ የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰንና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንት ጋሌማ ሞትላንቴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወደ ቀኝ፤ የቀድሞውን የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዮአኪም ቺሳኖ፣ የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰንና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንት ጋሌማ ሞትላንቴ

የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበርና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭትን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር እንዲወያዩ የተሰየሙት ልዑካን አዲስ አበባ መግባታቸው ተነገረ።

በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ግጭት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ በተሸጋገረበት ጊዜ ነው ሦስት የቀድሞ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ግጭቱ የሚያበቃበትን መንገድ ለመወያየት ወደ አዲስ አበባ የመጡት።

ልዑኩ የቀድሞውን የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዮአኪም ቺሳኖ፣ የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰንና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩትን ጋሌማ ሞትላንቴ የያዘ መሆኑ ተነግሯል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሕግን ማስከበበር ስለሆነ ከህወሓት አመራሮች ጋር ምንም አይነት ድርድር ለማድረግ ፍላጎት እንደሌለ ገልጸዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ወደ መቀለ ከተማ በቀረበበት ጊዜ የህወሓት አመራሮችና ተዋጊው ኃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ የተሰጠው የሦስት ቀናት ገደብ ረቡዕ ምሽት ማብቃቱን ተከትሎ መንግሥት የመጨረሻ ምዕራፍ ያለው ዘመቻ ሐሙስ ጠዋት መጀመሩን በገለጸበት ጊዜ ነው ልዑኩ አዲስ አበባ የገባው።

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሰየሟቸው ልዑካን መፍትሔ ለማፈላለግ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ የተገለጸው ባለፈው ቅዳሜ ሲሆን፤ ልዑካኑ በቀዳሚነት ግጭቱን ለማስቆም ከሁሉም ወገኖች ጋር በመነጋገር ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣትና "ግጭቱን ባስከተሉት ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለሚያስገኝ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ" ተብሎ ነበር።

ነገር ግን ልዑካኑ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ እንደተገለጸ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመንግሥት ስለጉዳዩ በተሰጠ መግለጫ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የሚልኳቸውን ልዩ መልዕክተኞች በግል ተቀብለው ከማነጋገር ውጪ ድርድር እንደማይኖር አመልክቷል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መንግሥታቸው እየወሰደ ያለው እርምጃ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ውስጥ የሚገኘው የሠሜን ዕዝ ላይ በትግራይ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ የሠራዊቱ አባላት እንደተገደሉና በካምፑ ውስጥ የነበሩ የጦር መሣሪያዎች እንደተዘረፉ በመግለጽ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ ከሦስት ሳምንት በላይ ሆኖታል።

ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ግጭቱ እንዲቆምና ውይይት እንዲጀመር በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ እየወሰደ ያለው "ሕግን የማስከበር እርምጃ" በመሆኑ ድርድር እንደማይኖር በተደጋጋሚ ገልጿል።

በዚህም መሰረት ተፈጸሙ ላላቸው ወንጀሎች ተጠያቂ የሆኑ የህወሓት አመራሮችን ለፍርድ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ በመሆኑ ለድርድር እንደማይቀመጥ አሳውቋል።

በትግራይ በኩል ያሉ ባለስልጣናት ግን እራስን በራስ የማስተዳደር መብታችንን ተጠቅመን ምርጫ በማካሄዳችንና መብታችንን በማስከበራችን የፌደራል መንግሥቱ ዘመቻ ከፍቶብናል ሲሉ ይከሳሉ።

በትግራይ ክልል የተከሰተው ቀውስ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የህወሓት ባለስልጣንት የአፍሪካ ሕብረትና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጣልቃ ገብተው እንዲያሸማግሏቸው ሲጠይቁ እንደነበር ይታወሳል።

በትግራይ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጡት ሦስት ቀናት እጅ መስጫ ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ በክልሉ ዋና ከተማ ላይ የመጨረሻ ያሉት ዘመቻ መጀመሩን ዛሬ ሐሙስ ጠዋት ይፋ አድርገዋል።