ትግራይ፡ በመቀለ አይደር ሆስፒታል ያለው ሁኔታ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, MU
በመቀለ ከተማ የሚገኘው ዋነኛው የህክምና ተቋም አይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሁኔታ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር አስታወቀ።
ሆስፒታሉ መደበኛ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጉት የነበሩት አቅርቦቶች በከፍተኛ ደረጃ በመሟጠጣቸው ህክምና ለሚፈልጉ ሰዎች አገልግሎቱን ለመስጠት አዳጋች ደረጃ ላይ መድረሱ ተገልጿል።
እስከ ትናንት ባለው መረጃ አይደር ሆስፒታል ድንገተኛና ህይወት አድን የሚባሉ ለምሳሌ ቀዶ ጥገናና የፅኑ ህሙማን ህክምና ለማቋረጥ መገደዱን የዓለም አቀፉ ቀይመስቀል የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ቃለ አቀባይ ክሪስታል ዌልስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቃለ አቀባይዋ ለዚህ እንደ ምክንያትነትም ያስቀመጡት መድኃኒቶች፣ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችና ነዳጅ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በማለቃቸው ነው ብለዋል። የተፈጠረውንም ችግር ለመቅረፍም ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር እየተወያዩ መሆኑንም አስረድተዋል።
"የህክምና ግብአቶችን ጨምሮ አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶችን አዲስ አበባ ካለው ክምችታችን ወደ መቀለ እንዲሄድ ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ላይ ነን። ይህንም በቅርቡ እንደሚፈፀም ተስፋ አለን" በማለትም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በመቀለ ከተማ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንዳጋጠመ ቀይ መስቀል በትዊተር ገፁ አስታውቋል።
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርም ጋር በመሆን ውሃ በከተማዋ ማከፋፈል መጀመራቸውን የገለፀው ድርጅቱ ይህም ሁኔታ ዋነኛው የውሃ አቅርቦት መስመር ሥራ እስኪጀመር ድረስ ይቀጥላል ብሏል።
"በእርግጠኝነት ይሄ ለከፍተኛ ችግር የተጋለጠውን የማኅበረሰቡን ህይወት የማዳን ተግባር ነው። ሁኔታውም አስጊ ደረጃ ላይ ነው" የሚል መልዕክት ድርጅቱ አስተላልፏል።
ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል በግጭቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ህክምና እየሰጠው ያለው አይደር ሆስፒታል አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ገልፆ ነበር።
ድርጅቱ እንዳለው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አምቡላንሶች በግጭቱ ሳቢያ የተጎዱና ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ወደ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል እያጓጓዙ ነው።
ሆስፒታሉን የጎበኙ የድርጅቱ ባልደረቦች "80 በመቶው ታካሚዎች በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። ሌሎች ሕክምናዎች ቆመው ለድንገተኛ አደጋ ብቻ አገልግሎት እየተሰጠ ነው" በማለትም ገልፆ ነበር።
የማኅበሩ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኃላፊ ማሪያ ሶልዳድ "ቁስል ለመስፋት የሚውል መገልገያ፣ ጸረ ተህዋሰ መድኃኒት፣ የህመም ማስታገሻ እና ሌሎችም መድኃኒቶች በአሳሳቢ ሁኔታ እያለቁ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የሞቱ ሰዎችን አስክሬን ማቆያ ፕላስቲኮች እየጨረሱ መሆኑንም ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ማኅበሩ ምን ያህል ሰዎች እንደተጎዱና እንደሞቱ ምንም መረጃ አልሰጠም። ተጎጂዎቹ ወታደሮች ይሁኑ ሲቪሎችም መሆናቸውም በወቅቱ አልተገለጸም።
ከሰሞኑም በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በቀጠለው ውጊያ ምክንያት እርዳታ ለማቅረብ የሚያደርገው ጥረት እንደተስተጓጎለበትም የተባበሩት መንግሥታት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
በክልሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው የምግብና የመድኃኒት ክምችት እተሟጠጠ መሆኑም ተነግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት ባለስልጣናት ለፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ ምንም እንኳን ያልተቋረጠ የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ቢደረስም ወደ አካባቢዎቹ መድረስ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ጭምር ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሠብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ ለዚህም ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "ነጻ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር" እንዲመቻች ጠይቀዋል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ለእርዳታ አቅርቦት ሠራተኞች የሚያገለግል መተላለፊያ መስመር እንደሚከፍቱ አስታውቀው ነበር።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተደረሰው ስምምነት የሚደረጉት የእርዳታ አቅርቦት ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት እንዲመራ ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትናንትናው ዕለት 18 ሺህ 200 ኩንታል የምግብ አቅርቦት የጫኑ 44 ከባድ የጭነት መኪኖችም ሽረ ከተማ መግባታቸውን ሰላም ሚኒስቴር በትዊተር ገፁ አስታውቋል።
ድጋፉ በሽረና በአቅራቢያው ባሉ ቦታዎችም እንደሚካሄድ መረጃው ጠቁሟል።
መንግሥት በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ያለው ወታደራዊ ዘመቻ ከተጀመረባት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በክልሉ የመብራት የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መቋረጡ የሚታወስ ነው።
ለሳምንት አገልግሎቱ ተቋርጦባቸው ከነበሩት አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው በአላማጣ ሙሉ በሙሉ የቴሌኮም አገልግሎት መጀመሩንና ኢትዮ ቴሌኮም ከሰሞኑ አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በምዕራብ በኩል በዳንሻ፣ በተርካን፣ ሁመራ፣ ሽራሮ፣ ማይካድራና ማይፀብሪም አገልግሎቱ በከፊል እንደተጀመረ ተገልጿል።
ወታደራዊ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ተቋርጠው የሚገኙትን የኤሌክትሪክ ኃይልና የቴሌኮም አገልግሎቶች መልሶ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት እነዚህን አገልግሎቶች መልሶ ለማስጀመር መቀለን፣ አክሱምና አዲግራትን ጨምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ቡድን መላኩን ጠቁመዋል።












