ትግራይ ፡ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦት ሥራን ሙሉ ለሙሉ እንደሚመራ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopia State of Emergency Fact Check Twitter pag
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተደረሰው ስምምነት የሚደረጉት የእርዳታ አቅርቦት ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት እንዲመራ ታሳቢ በማድረግ መሆኑ ተገለጸ።
ይህ የተነገረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲሆን በዚህ ሂደት የመንግሥት ሚና በማንም የሚተካ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
ይህንንም በተመለከተ አምባሳደር ሬድዋን በሰጡት ማብራሪያ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር የተደረሰው ስምምነት የሚካሄዱት የእርዳታ አቅርቦት ሥራዎች በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲመሩ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው "የትኛውም አካል የመንግሥትን ቦታ የሚተካ አይሆንም" ብለዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ጨምረውም በስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦቱን ሥራ በመምራት የሚያስተባብር ሲሆን የእርዳታ ድርጅቶቹ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ ስላለው ሁኔታ መንግሥት የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
"ኢትዮጵያ ኃላፊነቱን የሚወጣ መንግሥት ያላት አገር በመሆኗ ሞግዚት አያስፈልጋትም" ያሉት አምባሳደሩ መንግሥት አስፈላጊውን የምግብና የህክምና አቀርቦቶች እርዳታ አቅርቦት ለትግራይ ክልል የሚያቀርብ መሆኑን አማባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።
በዚሁ መግለጫ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ሰራተኞች እንደተተኮሰባቸውና በቁጥጥርም ስር እንደዋሉም አስታውቀዋል።
ጨምረውም መደረግ የነበረበት ነገር ሳይደረግ ቀርቷል ብሎ መንግሥት በሚያስብባቸው ሁኔታዎች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ይፈቅዳልም ብለዋል።
በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ከቤታቸው ሸሽተው ወደ ጎረቤት አገር እንደተሰደዱና ሌሎች ደግሞ እዚያው ሆነው ለችግር መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።
አነዚህ በአገር ውስጥ በችግር ላይ የሚገኙትን ሰዎች ለመርዳት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት አመቺ ሁኔታ እንዲፈጥር መስማማቱን ባለፈው ሳምንት ተገልጾ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ወታደራዊ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ተቋርጠው የሚገኙትን የኤሌክትሪክ ኃይልና የቴሌኮም አገልግሎቶች መልሶ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት እነዚህን አገልግሎቶች መልሶ ለማስጀመር መቀለን፣ አክሱምና አዲግራትን ጨምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ቡድን መላኩን ጠቁመዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የብሔራዊው የአደጋ ስጋት መከላከልና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ጨምረው እንደተናገሩት ከግጭቱ ቀደም ብሎ በትግራይ ክልል 1.8 የሚሆኑ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንደነበሩ ገልጸው፤ አሁንም እርዳታ ለማቅረብ ይኸው ቁጥር እንደመነሻ መያዙን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ ከሚገኙት ዝቅተኛ ነዋሪዎች መካከል ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑት የግብይት ስፍራዎች በአግባቡ ሥራ እስኪጀምሩ ድረስ የእርዳታ ድጋፍ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ወታደራዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለሳምንታት የዘለቀ ውጊያ መካሄዱ ይታወቃል። በዚህ ወቅትም ግጭቱን በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ትተው በአገር ውስጥና በጎረቤት አገር መጠለላቸውን የእርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ።
የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ስር ከገባች በኋላ መንግሥት በክልሉ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መጠገንና በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ በማቋቋም ላይ ከተለያዩ ተቋማት ጋር እንደሚሰራ መግለጹ ይታወሳል።
ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም እና አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር)
በፌደራል መንግሥቱ ከሚፈለጉት የህወሓት አመራሮች መካከል የሚገኙት አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) በቁጥጥሩ ስር እንዳሉም በዛሬው ዕለት በነበረው መግለጫ ተገልጿል።
አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ከመግለጽ ውጪ ስለተያዙበት ሁኔታ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።
በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች የት እንደሚገኙ ባይጠቁሙም ለፖሊስ ቃላቸውን መስጠታቸውንና ሕዝቡ "በቅርቡ" ግለሰቦቹ የሚሉትን እንደሚሰማ አመልክተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን በጠቀሱት መሰረት አዲስዓለም (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት እጃቸውን እንደሰጡ ከተነገረው የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም በመቀጠል በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ ሁለተኛው የህወሓት ከፍተኛ አመራር ናቸው።
አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) ከክልሉ ምክትል የርዕሰ መስተዳደርነት ስልጣን በተጨማሪ በተለያዩ የፌደራልና የትግራይ ክልል ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ ሲሆን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነውም ሰርተዋል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወንጀሎች እፈልጋቸዋለሁ ያላቸውን ከፍተኛ የህወሓት አመራሮችን ለመያዝ የእስር ትእዛዝ መውጣቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።












