ትግራይ ፡ በውጊያ ምክንያት እርዳታ ማቅረብ እንዳልቻለ የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ

ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች ግጭቱን ሸሽተው ወደ ሱዳን ተሰደዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች ግጭቱን ሸሽተው ወደ ሱዳን ተሰደዋል

በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በቀጠለው ውጊያ ምክንያት እርዳታ ለማቅረብ የሚያደርገው ጥረት እንደተስተጓጎለበት የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።

በክልሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው የምግብና የመድኃኒት ክምችት እተሟጠጠ መሆኑ ተነግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ባለስልጣናት ለፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ ምንም እንኳን ያልተቋረጠ የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ቢደረስም ወደ አካባቢዎቹ መድረስ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የመቀለ ከተማን ባለፈው ቅዳሜ ከተቆጣጠረና እየተካሄደ የነበረው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁ ከተገለጸ በኋላ ቢቢሲ ለመጀመሪያ ጊዜ በትግራይ ዋና ከተማ መቀለ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለማናገር ችሏል።

በሳተላይት ኢንተርኔት ያናገራቸው ምንጮች እንደሚሉት "ከመቀሌ አቅራቢያ በሚገኙ ስፍራዎች ላይ ውጊያ እየተካሄደ ነው" ብለዋል።

ቢቢሲ ያናገራቸውና ለደኅንነታቸው ሲሉ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈሉ ሁለቱ ግለሰቦች፤ በዚህ ሳምንት ረቡዕና ሐሙስ ራቅ ካለ አካባቢ የከባድ መሳሪያ ድምጽ መስማታቸውን ተናግረዋል።

ምንጮቹ ጨምረውም ከመቀለ ከተማ ምዕራብና ደቡብ አቅጣጫ የተኩስ ድምፅ መስማት እንደቻሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ ግንባታ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ዛዲግ አብረሃ ግን "ጦርነት እየተካሄደ አይደለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም "ህወሓት ጦርነት ማድረግ የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና የለውም" ሲሉ ገልጸዋል።

የህወሓት ኃይሎች ቃል አቀባይ ገብረ ገብረጻድቃን ረቡዕ እለት በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ከመቀለ ከተማ አቅራቢያ ባሉ ቦታዎች ላይ ውጊያ እያካሄዱ መሆኑን ተናግረው፤ "ጦርነቱ በቀላሉ የሚያበቃ አይደለም" ብለው ነበር።

'መቀለ ውስጥ መንግሥት የለም'

በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመሠረታዊ አገልግሎቶች እጥረት እየተቸገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ እንኳን ነዋሪዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን አመልክተዋል።

አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው "አሁን ድረስ በከተማዋ ውስጥ የውሃ፣ የመብራትና የባንክ አገልግሎት የለም።"

ነዋሪው ጨምሮም የከተማዋ ፖሊስና የጸጥታ ኃይል በሌለበት ሁኔታ ዘረፋ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ነው ብሏል።

"በከተማዋ ውስጥ መንግሥት የለም" በማለት የመንግሥት ወታደሮች ግን በተወሰኑ የተከማዋ ክፍል ውስጥ እንደሚታዩ ተናግሯል ።

በሌላ በኩል ግን ለኢትዮጵያ መንግሥት ቅርብ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን ከተማዋ "ወደ መደበኛ ሕይወት እየተመለሰች ነው" ሲሉ ዘግበዋል።

የአንድ ቤተሰብ አባላት ሞተውበታል የተባለው ቤት
የምስሉ መግለጫ, የአንድ ቤተሰብ አባላት ሞተውበታል የተባለው ቤት

'የሰላማዊ ሰዎች ሞት'

ባለፈው ቅዳሜ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ግማሽ ሚሊዮን የሚቆጠር ነዋሪ ያላትን የመቀለ ከተማን ከመቆጣጠሩ በፊት የከባድ መሳሪያ ድብደባ እንደነበር ተነግሯል።

በዚህም ሳቢያ አንዳንድ ነዋሪዎች ከጥቃቱ ለማምለጥ ወደ ከተማዋ ዳርቻ ሸሽተው ነበር።

ሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአገሪቱ ምክር ቤት ቀርበው እንደተናገሩት በዘመቻው "አንድም ሰላማዊ ሰው አልተገደለም" ብለዋል።

ነገር ግን ቢቢሲ ያናገራቸው የመቀለ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ቅዳሜ ዕለት ከተፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ በኋላ የቆሰሉና የሞቱ ሰላማዊ ሰዎችን ሆስፒታል ውስጥ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ከምንጮቹ መካከል አንደኛው የከባድ መሳሪያ ጥይት አይደር እዳጋ በጊ በተባለ የመኖሪያ አካባቢ ወድቆ የአንድ ቤተሰብ አባላትን መግደሉን ለቢቢሲ ገልጾ፤ በተጨማሪም ነዋሪው በጥቃቱ የወደመ ቤትና የቆሰሉ ሰዎችን የሚያሳይ ምስል አቅርቧል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት እንዳለው በመቀለ ከተማ የሚገኙ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት ከባለፈው ቅዳሜ ውጊያ በኋላ በርካታ የሞቱና የቆሰሉ ሰዎችን መቀበላቸውን ገልጿል።

የዲሞክራሲ ግንባታ ሚኒስትሩ ዛዲግ አብረሃ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ምላሽ "በእኛ በኩል ሙሉ በሙሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አድርገናል" ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ አጠናክረዋል።

'ጦርነቱ ይቀጥላል'

የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ውጊያው እየተካሄደ መሆኑን ይናገራሉ። በክልሉ የነበሩ ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ህወሓትን የሚደግፉ ዝግጅቶችን ከዚህ ቀደም ከሚያሰራጩበት ቦታ ውጪ ሆነው እያስተላለፉ ይገኛሉ።

የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ሐሙስ ምሽት በትግራይ ቴሌቪዥን ቀርበው "ጦርነቱ አልቆመም፤ ህልውናችንና ራስን የማስተደደር መብታችን እስካልተከበረ ድረስ ጦርነቱ አይቆምም" ብለዋል።

ነገር ግን ሚኒስትር ዛዲግ አብረሃ ጦርነቱ ማብቃቱን ለቢቢሲ ገልጸው "የቀረው ነገር የህወሓት መሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የመቀለ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ውስጥ የተካሄደው "ወታደራዊ ዘመቻ" እንዳበቃና አሁን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ሌሎች የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮችን ለመያዝ እያደነ መሆኑን ገልጿል።

የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ክልላቸውን "ወራሪዎች" ካሏቸው እየተከላከሉ መሆናቸውን አመልክተው ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች እንዲፈናቀሉና ወደ ሱዳን እንዲሰደዱ ያደረገው ለአንድ ወር በቆየው ውጊያ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።