ትግራይ ፡ አክሱም ተያዘና አውሮፕላን ተመታ መባሉን መንግሥት ሐሰት ነው አለ

አቶ ዛዲግ አብርሃ

የፎቶው ባለመብት, ADDIS FORTUNE NEWSPAPER

የህወሓት ኃይሎች ትላንት [እሁድ] ምሽት አክሱም ከተማ መልሰው እንደያዙና የፌዴራል መንግሥት ንብረት የሆነ ተዋጊ ጄት መትተው መጣላቸውን ገልጸው ነበር።

ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በህወሓት በኩል ተባሉት ነገሮችን "ነጭ ውሸት" ሲሉ አጣጥለውታል።

ሚኒስትር ዛዲግ ጨምረውም "የህወሓት የመጨረሻ ይዞታ የነበረችው መቀሌ ናት፤ ይህንን ሊያደርጉ አይችሉም" ሲሉ ተናግረዋል።

ከሦስት ሳምንት በላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ውስጥ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ዋና ከተማዋን መቀለን መቆጣጠሩን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መከላከያ "ሕግ የማስከበሩ ዘመቻ" መጠናቀቁን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከመቀለ መያዝ በኋላ ለሮይተርስ ዜና ወኪል በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እንደገለጹት በውጊያው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። በተጨማሪም የቡድኑ ኃይል መቀለ ከተማ አቅራቢያ ውጊያ እያካሄደ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ይህንን በተመለከተ ህወሓት የሽምቅ ውጊያ እያካሄደ እንደሆነ በቢቢሲ የተጠየቁት ሚኒስትሩ ዛዲግ አብረሃ ሲመልሱ "የህወሓት አመራሮች በአሁኑ ጊዜ ሕይወታቸውን ለማዳንና በሕግ ከመጠየቅ ለማምለጥ እየሸሹ ነው እንጂ ውጊያ ላይ አይደሉም" ሲሉ መልሰዋል።

ትናንት ምሽት ከየት ቦታ እንደሆነ ካልታወቀ ስፍራ ከህወሓት በኩል ወጣ በተባለ መግለጫ ላይ የቡድኑ ተዋጊዎች ከሳምንት በፊት በፌደራሉ ኃይሎች የተያዘችውን የአክሱም ከተማን መልሰው እንደተቆጣጠሩና አንድ ተዋጊ አውሮፕላን መትተው መጣላቸውን ገልጸዋል።

አቶ ዛዲግ አብርሃ ግን ተመትቶ የወደቀ የጦር አውሮፕላን እንደሌለና የአክሱም ከተማ "መያዝም በፍፁም ከእውነት የራቀ ነው" ብለው፤ "ህወሓት በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ወታደራዊ አቅም የለውም፤ ሚሊሻውም ሆነ ልዩ ኃይሉ እጅ እየሰጠ ነው" ሲሉ ከቢቢሲ ሬድዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አክለው በክልሉ ያለውን ሁኔታ ለጋዜጠኞች ክፍት ለማድረግ በትግራይ የተለያዩ ቦታዎች በርካታ መሠረተ ልማቶች በህወሓት ኃይል በመውደማቸው እነሱ ከተጠገኑ በኋላ ጋዜጠኞች ወደ ሥፍራው ሄደው ሁኔታውን ማጣራት ይችላሉ ሲሉ የመገናኛ መስመሮች አለመኖራቸውን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ዛዲግ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ሰዎች ትክክለኛው አሃዝ እንደሌላቸው አመልክተው፤ የቀሩት የህወሓት አመራሮች ሲያዙ ለሕግ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ያሉ የስልክና የኢንተርኔት መገናኛ መንገዶች የማይሰሩ በመሆናቸው ቢቢሲ ከክልሉ የሚወጡ መረጃዎችን በራሱ ማጣራት አልቻለም።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ህወሓት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመግባባት ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ መካረሩ ይታወሳል።

ተከትሎም የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ባለመቀበል ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደው የተናጠል ምርጫ የፌደራል መንግሥቱን ተቀባይነት ካለማግኘቱ በተጨማሪ በአገሪቱ ምክር ቤቶች ሕገ ወጥ ተብሎ ውድቅ ተደርጓል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የክልሉን አስተዳዳሪዎች ሕገ መንግሥቱን በመጣስና ከሕግ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል በማለት የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል ክልል አስተዳደር ጋር የነበረውን የቀጥታ ግንኙነት አቋርጦ የበጀት ዕቀባ ጥሎ ነበር።

አለመግባባቱና መካሰሱ ያለማቋረጥ በቀጠለበት ሁኔታ ጥቅም 24/2013 ዓ.ም ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ክልል በነበረው የፌደራሉ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ካደረጉ በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት በትግራይ ክልል ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ ይታወሳል።

መንግሥት "ሕግ የማስከበር" ባለውና ከሦሰት ሳምንታት በላይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ሰር ከዋለች በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አሳውቀዋል።