ትግራይ ውስጥ እርዳታ ለማቅረብ ከመንግሥት ጋር መስማማቱን ተመድ ገለፀ

የተፈናቀለች ህፃን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በግጭቱ በተጎዳችው ትግራይ ክልል እርዳታ ለማስገባት ፈቃድ መገኘቱንና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋርም ስምምነት መደረሱን አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊ አስታወቁ።

ሁኔታውን የሚገመግም የልዑካን ቡድንም በዛሬው እለት ህዳር 23/ 2013 ዓ.ም ሥራ እንደሚጀምርም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተባበሩት መንግሥታት ቃለ አቀባይ ሳቪያኖ አብሬውን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

በክልሉ በተለይ የምግብና የመድኃኒት እጥረት እንዳጋጠመና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩም ተቸግረው እንደሚገኙም ተገልጿል።

በመቀለ ከተማ የሚገኘው አይደር ሪፈራል ሆስፒታል አስፈላጊ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶች እያለቁበት እንደሆነም ከሰሞኑ ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማልበር አስታውቋል።

በግጭቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ሕክምና እየሰጠ ያለው ሆስፒታሉ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የስደተኛ ማቆያዎች ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች የምግብ እጥረት እያጋጠማቸው እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት የስደተኞች ተቋም ዩኤንኤችሲአር ገልጿል።

ተቋሙ ለስደተኞቹ አስፈላጊውን አቅርቦት ለማድረስ የሚያስችለው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አቅርቦት መንገድ እንዲከፈትም ጠይቋል።

ከሳምንታት በፊት በትግራይ ክልል ኃይል እና በፌዴራል መንግሥት ሠራዊት መካከል ወታደራዊ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ በክልሉ የመገናኛ መስመሮችና እርዳታ የሚገባባቸው መንገዶች ተዘግተዋል።

ለአንድ ወር በላይ በዘለቀው ወታደራዊ ግጭት ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፤ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው እተነገረ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የክልሉ መዲና መቀለ በመከላከያ ቁጥጥር ስር እንደዋለች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስታውቆ ነበር።

ነገር ግን የህወሓት ኃይሎች አሁንም በከተማዋ አቅራቢያ እየተዋጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተባበሩት መንግሥታትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተደረሰው ስምምነት ምንድን ነው?

የተባበሩት መንግሥታት የፌደራል መንግሥት በሚቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል ያለምንም እክል እርዳታ እንዲያቀርብ መስማማታቸውን የዜና ወኪሎች ሪፖርት አድርገዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድርጅት ቃለ አቀባይ ሳቪያኖ አብሬው እንዳሉት ስምምነቱ በዚህ ሳምንት ከተፈረመ በኋላ የመጀመሪያው ስራ የሚሆነው የሚያስፈልጉ የእርዳታ አቅርቦቶችን መገምገም ነው በማለትም ይህ ስራም ረቡዕ ይጀመራል ብለዋል።

" በአጠቃላይ በክልሉ እንዲሁም እርዳታ ለሚያስፈልገው ማንኛውም ሰው እርዳታ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራን ነው" በማለትም ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናግረዋል።

በሌላ መልኩ ቃለ አቀባዩ የተባበሩት መንግሥታት ከመንግሥት ጋር በመሆን እርዳታን ለማቅረብ የሎጂስቲክስ ቡድን ማቋቋሙን ለሮይተርስ የተናገሩ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስምምነት መደረሱን አስመልክቶ ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ መንግሥት ለችግር የተጋለጡ ሰዎችን ለመርዳት የእርዳታ አቅርቦት መስመር እንደሚያመቻችና ከዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ጋርም በጋራ እንደሚሰራ አሳውቆ ነበር።