ትግራይ ፡ በትግራይ ያሉ ኤርትራዊያን ስደተኞች የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል ተባለ

ኤርትራውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, IOM

የምስሉ መግለጫ, ኤርትራውያን ስደተኞች

ከሦሰት ሳምንታት በላይ ወታደራዊ ግጭት በተካሄደባት ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ የስደተኛ ማቆያዎች ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች የምግብ እጥረት እያጋጠማቸው እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ዩኤንኤችሲአር አስታወቀ።

ተቋሙ ለስደተኞቹ አስፈላጊውን አቅርቦት ለማድረስ የሚያስችለው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አቅርቦት መንገድ እንዲከፈት ጠይቋል።

በትግራይ ክልል ኃይል እና በፌዴራል መንግሥት ሠራዊት መካከል ወታደራዊ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ በክልሉ የመገናኛ መስመሮችና እርዳታ የሚገባባቸው መንገዶች ተዘግተዋል።

እንደ ድርጅቱ መረጃ በትግራይ ክልል ውስጥ 100 ሺህ የሚሆኑ ኤርትራውያን በአገራቸው ያለውን ፖለቲካዊ እስርና አስገዳጅ የግዳጅ የውትድርና ሥልጠና በመሸሽ ተሰደው ይገኛሉ።

ከኤርትራውያኑ ስደተኞች የምግብ እጥረት ጉዳይ በተጨማሪ ከተቀሰቀሰ አንድ ወር ሞላውን ወታደራዊ ግጭትን በመሸሽ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች መሥሪያ ቤት አክሎም "ኤርትራውያን ስደተኞች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው፤ ታፍነው እየተወሰዱ ነው" የሚሉ ያልተጣሩ ዘገባዎችን ተከትሎ ስጋት ላይ ነኝ ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የመቀለ ከተማ በፌደራል ሠራዊቱ ቁጥጥር ሥር መዋሏን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሚካሄደው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ተጠናቋል ማለታቸው ይታወሳል።

ነገር ግን የህወሓት ሊቀ መንበር የሆኑት ደብረፂዮን ገብረሚካዔል አሁንም ጦርነት እንዳለና ኃይላቸው ድል እያገኘ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ይህንን በእራሱም ሆነ ከሦስተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

ረሃብ

ጄኔቫ ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት መግለጫ የሰጠው የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም (ዩኤንኤችሲአር) ጊዜው እየገፋ በሄደ ቁጥር ትግራይ ክልል ያሉ የኤርትራውያን ስደተኞች ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እየወደቀ ነው ብሏል።

"መጠለያ ካምፖች የምግብ እጥረት እየገጠማቸው ነው። ረሃብና ያልተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እያንዣበበ ነው። ትግራይ ክልል ግጭት ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ ስለዚህ ጉዳይ ማስጠንቀቂያ ስንሰጥ ነበር" ይላል መግለጫው።

አክሎም "በጣም የሚያስጨንቀን ጉዳይ በካምፖች አካባቢ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑና ጥቃቶች መሰማታቸው ነው። ስተደኞች በግድ ታፍነው እየተወሰዱ እንደሆነም ሰምተናል። ስለዚህ ወደዚያ ሄደን ሁኔታውን ራሳችን እንድናጣራ መንገድ ሊከፈትልን ይገባል" ሲል መግለጫው ያትታል።

ድርጅቱ አክሎም ሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ እንዲደርግላቸው ጥሪ አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባለፈው ሰኞ ለአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ስለወቅታዊ ጉዳዮች በሰጡት ማብራሪያ ላይ በግጭቱ መንግሥት አንድም ንፁህ ዜጋ እንዳልገደለ ተናግረዋል።

መንግሥት ለሰብዓዊ እርዳታ የሚሆን በር እንደሚከፍትም አስታውቋል።

በፌደራል መንግሥቱ የሠሜን ዕዝ ላይ በትግራይ ክልል ኃይሎች አማካይነት የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ከሦሰት ሳምንታት በኋላ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ባለፈው ቅዳሜ በመንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ስር መዋሏ ይታወሳል።

በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ክልሉን መልሶ በመገንባትና የተፈናቀሉትን ወደቀያቸው በመመለስ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።