ትግራይ ፡ የቀድሞው የሠሜን ዕዝ አዛዥ ሳይመረዙ እንዳልቀሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE
በሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት የዕዙ አዛዥ ሳይመረዙ እንዳልቀረ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዳሉት፤ የሠሜን ዕዝ አዛዥ የነበሩት ጄነራል ድሪባ ግጭቱ ከመፈጠሩ ከሁለት ሳምንት በፊት "ስብሰባ ከእነሱ ጋር ውሎ፣ ምሳ ከበላ በኋላ ታሞ እራሱን ስቶ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ገብቷል" ብለዋል።
ጨምረውም ከጄነራሉ ጋር የነበሩ ሰዎች "አቅምሰውት ነው" የሚል መረጃ እንዳመጡና እንዲህ ያለው ጉዳይ በህክምና እስኪጣራ ድረስ እንዲቆይ "ብለን አፈንነው" ካሉ በኋላ፤ ጄነራል ድሪባ ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት አስካሁን አገግመው ወደሥራቸው እንዳልተመለሱ ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ጄነራሉን በመተካት የሠሜን ዕዝን የሚመራ ጄነራል ለመመደብ መገደዳቸውንና የህወሓት አመራሮች አዲሱን ተሿሚ አንቀበልም ማለታቸውን በመግለጽ "ለካ እሱን በማኮላሸትና የሚመጣውን እምቢ የማለት ፍላጎት ነበረ" ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህም በኋላ "የሠሜን ዕዝ አዛዥ ጄነራል ድሪባ ታመሙ፣ አዲስ የተመደበውን ጀነራል አንቀበልም አሉ ከዚያም ጥቃት ፈጽመው የዕዙን ምክትል አዛዥ ጀነራል አደምን አፈኑ" ሲሉ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ከምክር ቤቱ አባላት ስለወቅታዊ ጉዳዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ላይ ነው።
የአገሪቱ ከፍተኛው ሠራዊትና የመከላከያ መሳሪያዎች ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የሠሜን ዕዝ ስር እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ቀደም በርካታ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች በህወሓት በኩል ተደርጎ ነበር በማለት፤ "በተደጋጋሚ መሳሪያውን ለማስወጣት ጥረት ቢደረግም ፈቃደኛ አልሆኑም" ብለዋል።
በመጨረሻም ጥቅምት 24/2013 ዓ. ም ምሽት 5 ሰዓት 30 አካባቢ በሠራዊቱ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው፤ በእሳቸው ትዕዛዝም መጀመሪያ ጥቃትን መከላከልና ወደ ጎንደርና ወልዲያ እንዳይስፋፋ ለማድረግ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል።
ስለ ወቅታዊ ሁኔታ
ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የመከላከያ ሠራዊት መቀለ እና ሌሎችም የትግራይ ከተሞችን እንደተቆጣጠረ ገልጸው በዘመቻው "አንድም ንጹህ ሰው አልተገደለም" ብለዋል።
ቀጣዩ እርምጃ በክልሉ አመራር ላይ የነበሩ የህወሓት አባላትን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ እንደሆነም አክለዋል።
አያይዘውም፤ ዘመቻውን አስታኮ እየተገለጹ ያሉ የደስታ መግለጫዎች ቀና የሆነ መንገድ እንዲላበሱ አሳስበዋል።
ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተለያዩ አገሮች ድርድር እንዲያሄዱ ሲጠይቁ እንደነበር አስታውሰው፤ አንዳንዶቹ ለአገሪቱ በጎ ከማሰብ ቢሆንም አንዳንዶች ግን ውስጣዊ ችግርን ለመፍታት ይሳናቸዋል ከሚል የተሳሳተ እሳቤ የተነሱ መሆናቸውን አስምረውበታል።
እንደ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያና ሱዳን ያሉ አገሮችን ጠቅላይ ሚንስትሩ ያመሰገኑ ሲሆን፤ በተለይ ከኤርትራ ጋር ሰላም መውረዱ ከወቅታዊው ሁኔታ አንጻር ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር አስረድተዋል።
ግጭቶች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ ብቻ በአገሪቱ ሆን ተብሎ የተቀሰቀሱ 113 ግጭቶች መከሰታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ ግጭቶች ብሔርንና ሐይማኖትን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውንና ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ እንደተከሰቱ አመልክተው፤ ከእነዚህ በርካታ ሰዎች ከሞቱባቸውና ከፍተኛ ንብረት ከወደመባቸው ግጭቶች ጀርባ የሥልጣን የበላይነትን መልሰው ለመያዝ ሲጥሩ የነበሩት የህወሓት አመራሮች እንዳሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ከእነዚህ ግጭቶች መካከል በኦሮሚያ 37፣ በአማራ 23፣ በጋምቤላ 7፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ፣ በቤኒሻንጉል፣ በደቡብ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በድሬዳዋ፣ በሐረሪና በሲዳማ በክልሎች እንደሆነ አመልክተዋል።
ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ሰፊ የቀውስ ዕቅድ ነበረ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ዕቅድ ተጨማሪ አስር የሚደርሱ ሌሎች ሰዎች በመግደል፣ ግድያውን የብሔር መልክ በማስያዝ ከባድ ጉዳት ለማድረስ ታስቦ እንደነበረ ተናግረዋል።
ይህ የምክር ቤቱ ስብሰባ የተካሄደው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህወሓት ኃይሎች በአገሪቱ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸው፤ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ ከሦስት ሳምንታት በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት ዋና ከተማዋን ጨምሮ ትግራይን መቆጣጠሩን ካሳወቀ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ባለፉት ሳምንታት በትግራይ ክልል የተከሰተው ቀውስ ላይ አተኩረው ከምክር ቤቱ አባላት የቀረቡትን ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ በሰጡት ማብራሪያ ላይ በአገሪቱ የለውጥ እርምጃዎች መወሰድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥታቸው የገጠመውን ፈተና በዝርዝር አስረድተዋል።
በለውጡ ሰሞን ስለተከሰቱ ነገሮች
መንግሥት ቀደም ብሎ በህወሓት ላይ እርምጃ መውሰድ ቢችል ኖሮ አሁን በትግራይ ውስጥ ያጋጠመውን አይነት ቀውስ ለማስቀረት ይቻል ነበር በማለት ከምክር ቤቱ አባላት ለተሰጠው አስተያየት ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለውጡ ከመጀመሩ በፊትና ከጀመረ በኋላም ከባድ ፈተናዎችን እንደተጋፈጡ ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት የአገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን ይዘው ከነበሩ የደኅንንትና የመከላከያ አመራሮች እሳቸውን ጨምሮ ለውጥ እንዲመጣ ጥረት ሲያደርጉ በነበሩት ሰዎች ላይ ውንጀላዎች፣ ማሳደዶችና ግድያ ለመፈጸም መከራና ማዋከብ ነበረ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በለውጡ ሰሞን በስልጣን ላይ የበላይ ሆኖ ለመቀጠል ፍላጎት የነበረው ቡድን በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ላይ መፈንቅለ መንግስት ለማደረግ ሲያሴር እንደነበረ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ ሲያሳውቁ ደግሞ እየታዘዘ በታማኝነት ቦታውን የሚይዝ ሰው ለመተካት ጥረት ሲደረግ ነበር ብለዋል።
በዘህም ሳቢያ ከእነሱ ፈቃድ ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ሰዎችን ተስፋ ለማስቆረጥና ለማስወገድ በደኅንነቱና በታጠቁ ወታደሮች ከባድ ክትትል ይደረግባቸው እንደበር አመልክተዋል።
በዚህም ስጋት ውስጥ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩና አጋሮቻቸው በገዢው ኃይል በወቅቱ እስር ወይም ግድያ ቢፈጸምባቸው ትግሉ እንዲቀጥልና ያለውን ሁኔታ የሚያመልክቱ የቪዲዮና የጽሁፍ መልዕክቶች አዘጋጅተው በሚታመኑ ሰዎች እጅ እንዲቀመጥ እስከማድረግ ተገደው እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህ ሁኔታው ውስጥ እንዳሉም ከመመረጣቸው ከቀናት ቀደም ብሎ የለውጡ መሪዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ወጥቶባቸው እንደነበርና፤ ከዚያ በፊት ግን ከጦርነት ያልተናነሰ ውዝግብ ተካሂዶ ምሽት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ለማድረግ በምርጫ በድምጽ ሲወሰን ቡድኑ "የመጀመሪያው ሽንፈት አጋጠማቸው" ሲሉ አብራርተዋል።
የህወሓት አመራሮች ፍላጎት የነበረው "እኛን በማስወገድ መንግሥት ያልሆኑ ግን መንግሥት የሚመስሉ ሰዎችን ማስቀመጥ ነበር፤ በመቃብራችን ላይ ነው እኛ ያማንፈልገው ሰው አገርን የሚመራው ሲሉ ነበር" በማለት የነበረውን ሁኔታ ገልጸውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ
ከለውጡ በኃላ በአዲስ አስተሳሰብ ቂምና ጥላቻን በመተው በይቅርታ ላይ የተመሰረተ አካሄድን በመከተል "አቃፊ አገረ መንግሥት እንገንባ የሚል ሀሳብ ለማራመድ ተሞክሯል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ይሁን እንጂ በስብከት አገር መምርት አይቻልም፣ ደካማ መንግሥት ነው ያለው በሚል እሳቤው በተፈለገው መንገድ ለውጥ ሊያመጣ አልተቻለም" ብለዋል።
ጫናውና ክትትሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላም መቀጠሉን የሚናገሩት ዐብይ፤ በተሾሙበት ዕለት የግል ጠባቂዎቻቸውን ወደ ጽህፈት ቤታቸው ይዘው መግባት እንደማይችሉ በአገሪቱ ደኅንነት ሹም እንደተነገራቸው በመጥቀስ "በወቅቱ እንኳንስ አገር ልመራ፤ የግል ጠባቂዎቼን እንኳን ማዘዝ አልችልም ነበር" ብለዋል።
ቤታቸውና ጽህፈት ቤታቸው በደኅንነት ሠራተኞች ቁጥጥጥር ስር በመሆኑ በነጻነት የዕለት ከዕለት ስራቸውን ለመስራት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደነበሩ "እንኳንስ የአገርን ደኅንነት ልጠብቅ ይቅርና የልጆቼን ደኅንነት እንኳን ማረጋገጥ በማልችልበት ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ" ሲሉ ምን ያህል የአገሪቱ የደኅንነት ተቋም ከሕግ በላይ እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህም ሳቢያ በወቅቱ "ዘመናዊ እስር ቤት ውስጥ የነበረ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆኔን ተረዳሁ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መታፈን መገደል ሊያጋጥም ይችላል በሚል ለቤተሰባቸው ደኅንንት በመስጋት ቀድሞ ወደሚኖሩበት አገር እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የታቀደ ሥራን መጀመር
ከለውጡ በፊትና በለውጡ ሰሞን ከባድ ያለመረጋጋት ችግር ገጠመው የሶማሌ ክልል ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንደጀመሩ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገሪቱን ለማናጋት የሚፈልገው ቡድን የሶማሌ ክልልን ማዕከል በማድረጉ ይህንን ችግር ለመፍታት ወደ ክልሉ ለመሄድ ባሰቡ ጊዜ የደኅንንት ሹሙ "አልሻባብ ይገድልሀል መሄድ አትችልም ተባልኩ፤ ነገር ግን ሥራዬን ልስራ ብዬ ሄድኩ" ይላሉ።
በመቀጠልም፤ "ወደ መቀለ ስሄድ የሕዝቡ አቀባበል ድንጋጤ ፈጠረባቸው፣ አምቦ፣ ባሕር ዳር ለመሄድ ስነሳ ኦነግና የቅማንት ኮሚቴ ይገድልሃል ተባልኩ ነገር ግን አልቀረሁም" በማለት ደኅንነቱ አገሪቱን ለማረጋጋት በሚሰሩ ሥራዎች ውስጥ ሁሉ ጣልቃ ሲገባ እንደነበር ሌሎች ምሳሌዎችንም በመጥቀስ የነበረውን ፈተና አስቀምጠዋል።
የአገሪቱ የመከላከያና የደኅንነት ተቋማት የአንድ ቡድን መጠቀሚያ በመሆናቸው ከዚያ በኋላ በእንዲህ አይነት ሁኔታ መቀጠልና አገርን መገንባት አስቸጋሪ መሆኑ በመታመኑ ከሌሎች የለውጡ አመራር አባላት ጋር በመሆን በጥናት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ "በመከላከያና በደኅንነቱ ውስጥ ያሉትን በመንግሥት ውስጥ ያሉ መንግሥታትን የማንሳት ውሳኔ ላይ ተደረሰ" በማለት ለውጥ እንደተጀመረ ገልጸዋል።
ለውጥ በመከላከያ
በአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያለው አብዛኛው የአመራርነት ቦታ ከትግራይ በመጡ ሰዎች የተያዘ በመሆኑ በአሃዝ አስደግፈው ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ይህ በተገቢው ልክ መሆን ይኖርበታል ተብሎ የለውጥ ሥራ ተጀምሯል። ኢትዮጵያን የሚመስል መከላከያ ሠራዊት ለመገንባት እየተሰራ ነው" ብለዋል።
ባለፉት ሦስት አስርታት ሠራዊቱ የአንድ ፓርቲ መመሪያን ይከተል ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ እንደ አብነትም የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት መመሪያን አንስተው "ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረንና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮትን በመጠበቅ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነበር" ብለዋል።
በዚህም መሠረት ባለፉት ሁለት ዓመታት የመከላከያ ሠራዊቱ ላይ መንግሥት ሰፊ የለውጥ እርምጃ ማድረጉን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይ እጅግ ወሳኝ ተልዕኮዎችን የሚወጣ ልዩ ኃይል (ስፔሻል ፎርስ) እና አየር ኃይል ላይ ሰፊ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሠራዊቱ ላይ ከተደረገው ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ሪፐብሊካን ዘብ (ሪፐብሊካን ጋርድ) አስፈላጊነቱ እያበቃ ስለሆነ ወደ መከላከያው እንደሚካተት አስታውቀዋል።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመግባባት ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ መካረሩ ይታወሳል።
ተከትሎም የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ባለመቀበል ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደው የተናጠል ምርጫ የፌደራል መንግሥቱን ተቀባይነት ካለማግኘቱ በተጨማሪ በአገሪቱ ምክር ቤቶች ሕገ ወጥ ተብሎ ውድቅ ተደርጓል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የክልሉን አስተዳዳሪዎች ሕገ መንግሥቱን በመጣስና ከሕግ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል በማለት የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል ክልል አስተዳደር ጋር የነበረውን የቀጥታ ግንኙነት አቋርጦ የበጀት ዕቀባ ጥሎ ነበር።
አለመግባባቱና መካሰሱ ያለማቋረጥ በቀጠለበት ሁኔታ ጥቅም 24/2013 ዓ.ም ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ክልል በነበረው የፌደራሉ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ካደረጉ በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት በትግራይ ክልል ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል።
መንግሥት "ሕግ የማስከበር" ባለውና ከሦሰት ሳምንታት በላይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደዋል።
ባለፈው ቅዳሜ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ሰር ከዋለች በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አሳውቀዋል።















