የሳተላይት ምስል፡ አክሱም አየር ማረፊያ ከጥቃቱ በፊት እና በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Planet Labs
ከመቀለ ከተማ በሰሜን አቅጣጫ የሚገኘው የአክሱም አየር ማረፊያ በትግራይ ውስጥ ቁልፍ ስፍራ መሆኑ ይታመናል።
መንግሥት አየር ማረፊያውን ከመቆጣጠሩ በፊት የትግራይ ኃይሎች የአየር ማረፊያው መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል።
በትግራይ የቴሌኮም አገልግሎቶች ስለተቋረጡ በስፍራው ምን እየተከናወነ እንደሆነ ማረጋገጥ ከባድ ሆኖ ቆይቷል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ያስራጩትን ተንቀሳቃሽ ምስል፣ የሳተላይት ምስሎችን ጋር በማዛመድ በአክሱም አየር ማረፊያ መቼ ምን እንደተከሰተ ለማጣራት ጥረት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አክሱም አየር ማረፊያን መቆጣጠሩን ከማስታወቁ በፊት አየር ማረፊያው በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ቆይቷል።
በዚህም ሐሙስ ኅዳር 10 የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ለሮይተርስ ዜና አገልግሎት አክሱም ከተማ በቁጥጥራቸው ሥር እንደምትገኝ ተናግረው ነበር። ይህ ግን የአክሱም አየር ማረፊያን እንደሚጨምር ገልጽ አይደለም።
"አክሱም ከእኛ ጋር ነች- ግን አክሱምን ለመቆጣጠር የተላከ ጦር አለ- ጦርነት አለ" ብለው ነበር ደብረጽዮን።
የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ከተሞችን ከህወሓት ኃይሎች ሲያስለቀቅ የህወሓት ኃይሎች በከተሞቹ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እያደረሱ እየሸሹ እንደሆነ አስታውቋል።
እሑድ ኅዳር 13 የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የአክሱም አየር ማረፊያ አውሮፕላን መንደርደሪያ ተቆፋፍሮ እና በድንጋይ ተሞልቶ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አሳይተዋል።
መንግሥት "ለአክሱም ከተማ እና ለአከባቢዋ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝ የነበረውን አየር ማረፊያ እንዲወድም ተደርጓል" ሲልም ከሷል።

ይህ ለማረጋገጥም ቢቢሲ የሳተላይት ምስሎችን ተመልክቷል። የሳተላይ ምስሎቹ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አክሱም አየር ማረፊያን ከመቆጣጠሩ በፊት እና ከተቆጣጠረ በኋላ ያለውን ልዩነት ያመለክታል።
ከዚህ በተቻ ያለው ምስል የአክሱም አየር ማረፊያ ሐሙስ ኅዳር 10 ያሳያል። የሳተላይት ምስሉ ኅዳር 10 አክሱም አየር ማረፊያ ጉዳት እንዳልደረሰበት ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት, Planet Labs
ሰኞ ኅዳር 14 የተነሳው የሳተላይ ምስል ግን በአየር ማረፊያው ላይ ጉዳት መድረሱን ያስመለክታል።
ምስሉ የአየር መንገዱ አውሮፕላን መንደርደሪያ አስፋልት አውሮፕላን ማረፍ እንዳይችል ሦስት ቦታዎች ላይ ተቆፍሮ የሚታይ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም አውሮፕላን ማረፊያው መንደርደሪያ በድንጋይ ተሞልቶ ይታያል።
ይህም ቀደም ባለው ቀን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ያሉትን የሚያረጋግጥ ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Planet Labs
የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ግን ህወሓት በአየር ማረፊያው ላይ ጉዳት አለማድረሳቸውን አስተባብለዋል። ይሁን እንጂ የአገር መከላከያ ሠራዊት የወደፊት ጉዞን ፍጥነትን ለመግታት እክል ማድረጋቸውን አምነዋል።
ከአየር ማረፊያው ጋር ተያይዘው የወጡ ሐሰተኛ ምስሎች
በትግራይ የቴሌኮም አገልግሎቶች ተቋርጠው ስለሚገኙ በስፍራው እየተፈጠረ ያለውን በትክክል የሚያመለክቱ ምስሎችን ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
ይህም ሐሰተኛ ምስሎች በስፋት እንዲሰራጩ ምክንያት ሆኗል።
መንግሥት አክሱም ከተማን እና አየር ማረፊያውን መቆጣጠሩን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የመንግሥት ደጋፊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የቆዩ ወይም አክሱም አየር ማረፊያ ያልሆኑ ምስሎችን ሲያጋሩ ነበር።

ይህም ብቻ ሳይሆን የአየር ማረፊያው ተጓዞች መቆያ ቦታ (ተርሚናል) ጉዳት ደርሶበታል በሚል ከታች ያለው ምስል በስፋት ተጋርቷል።
ይህ ከዚህ በታች ያለው ምስል የተወሰደው እአአ 2014 ላይ ጉዳት የደረሰበት የሊቢያ አየር ማረፊያ ነው።

የአክሱም አየር ማረፊያ ለምን ወሳኝ ሆነ?
ኢትዮጵያ ሰፊ የሆነ የቆዳ ስፋት ያላት አገር በመሆኗ ጦር ሠራዊቱን እና ግብዓቶቹን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ አየር ማረፊያዎች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።
በባልሲሌ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጄራል፤ "አክሱም አየር ማረፊያ ትልቅ ጥቅም አለው። አየር ማረፊያዎች ወታደሮችን ለማጓጓዝና የግንኙነት መስመርን ክፍት ለማድረግ አስፈላጊዎች ናቸው። ሌሎች በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙት የባሕር ዳር እና ጎንደር አየር ማረፊያዎች በደሰረባቸው ጥቃቶች ጉዳት አጋጥሟቸዋል።
"የክልል ኃይሎች አየር ማረፊያውን መቆጣጠር ካልቻሉ ጥቅም ላይ እንዳይውል የማድረግ ዘዴን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ይህም ስጋት ሲያይልባቸው እንደመጨረሻ አማራጭ የሚወሰድ ነው" ብለዋል።















