ኮሮናቫይረስ፡ ኤርትራውያን ስደተኞች ስጋት በኢትዮጵያ

"ስደተኞች መመዝገብ ተከልክሏል፤ ወደ አገራችሁ ተመለሱ።"
"አንመለስም።"
"አንመለስም ካላችሁ ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ ትገባላችሁ። ሙሉ ወጪያችሁንም እራሳችሁ ትሸፍናላችሁ።"
"ገንዘብ የለንም።"
"ኋላ ላይ ተቸገረን እንዳትሉ አስቀድመን እየነገርናችሁ ነው።"
"ምርጫ የለንም፤ እኛም አሁን እንደማንመለስ እየነገርናችሁ ነው።"
ይህ ምልልስ ኢትዮጵያና ኤርትራን በሚያዋስነው ራማ-ክሳድ ዒቃ ድንበር በኤርትራውያን ስደተኞችና በኢትዮጵያውያን ድንበር ጠባቂዎች መካከል የተደረገ ነው።
ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጇ ይታወሳል፤ ማንኛውም ከሌላ አገር የሚመጣ ሰው ደግሞ ለ14 ቀናት መንግሥት ባዘጋጃቸው ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ገብቶ መቀመጥ እንዳለበት ተደንግጓል።
በማቆያ ማዕከሉም የራሱን ወጪ መሸፈን እንዳለበት ከዚህ ጋር ተያይዞ ተነግሯል። በእርግጥ በአዲስ አበባ አቅም ለሌላቸው ተመላሾች የከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጀው መቆያ እንዳለ ተገልጿል። ይህ ግን በአዲስ አበባ እንጂ በትግራይ የለም።
በድንበር በኩል ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው ለሚመጡ ሰዎች በአካባቢው እራሳቸውን ለይተው የሚያቆዩባቸው የተዘጋጁ ማዕከላት የሉም። በየዕለቱ በርካታ ኤርትራውያን ድንበር እያቋረጡ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ።
በቅርቡ ኢትዮጵያና ኤርትራን በሚያዋስነው ራማ-ክሳድ ዒቃ የገቡት ኤርትራውያን ስደተኞች፤ በአንድ ግንባታው ያላለቀ ህንጻ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ቢቢሲ ያናገራቸው ስደተኞች ይገልጻሉ። እነዚህ ስደተኞች ስማቸው እንዳይገለፅ ቢቢሲን ጠይቀዋል።
የከተማዋ ሕዝብ በተቻለው መጠን ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ ለቢቢሲ የገለፁት እነዚህ ስደተኞች፣ አቶ ተክኤ የተባሉ አንድ የከተማዋ ኗሪ በርካታ ገንዘብ አውጥተው እንደደገፏቸው ይገልጻሉ።
ሆኖም ከእለት ወደ እለት ቁጥራቸው እየጨመረ ስለመጣ ሁሉንም በግል አቅማቸው ብቻ ለመርዳት እንደተቸገሩና የሚመለከተው አካል ኃላፊነት ወስዶ እንዲረዳቸው መጠየቃቸውን ያስረዳሉ።
በስፍራው ለሁለት ሳምንታት የቆዩት ደግሞ፤ የትግራይ ክልል መንግሥት በደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ከከተማ ወደ ከተማ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ፤ በሌላ ግንባታ ላይ ባለ ህንጻ ውስጥ መቀመጣቸውን ገልፀዋል።

አንዳንዶቹም ቢሆኑ በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የሻይ ቤቶች ተጠግተው በርካታ ቀናቶች እንዳሳለፉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በሌላም በኩል ደግሞ፤ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ሸራሮ ከተማ፣ 300 የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።
በሸራሮ ከተማ እንኳን ለስደተኞች ለአካባቢው ኗሪም ለቀላል በሽታዎች እንኳ የሚውል የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት መኖሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የከተማዋ ነዋሪ ያስረዳል።
"ለራስ ምታት ሆነ ለተቅማጥ የሚሆን መድኃኒት ባለመኖሩ፤ ስደተኞቹ ችግር ላይ ናቸው" በማለት ለቢቢሲ የተናገሩት እኚህ ግለሰብ፣ "ከሁሉም በላይ ግን ከባድ የውሃ እጥረት ችግር አለ" በማለትም አክለዋል።
በዚህ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት እጅን ደጋግሞ በውሃና ሳሙና መታጠብ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት፤ በትግራይ ክልል ስደተኞቹ በሚገኙባቸው ስፍራዎች ሁሉ የውሃ እጥረት መኖሩን ቢቢሲ ካነጋገራቸው ሰዎች መረዳት ችሏል።
ስደተኞቹ በሚጠለሉባቸው ጣቢያዎች፤ በአንድ ቤት ውስጥ በርከት ያሉ ሰዎች በጋራ ስለሚኖሩ በዚህ በሽታ የታመመ ሰው ቢኖር ለይቶ ለማቆየትም ሆነ ለመከላከል ያላቸው እድል ጠባብ መሆኑንም ጨምረው ያስረዳሉ።
በመሆኑም ስደተኞቹ የመሰረታዊ ሸቀጦች መወደድና ለይቶ ማቆያና ማከሚያ ያለመኖር ከሚያሳስባቸው ይልቅ፤ የውሃ እጥረት ከልክ በላይ እንደሚያስጨንቃቸው ገልፀዋል።
ኤርትራውያን ስደተኞች ከሚገኙባቸው የመጠለያ ጣቢያዎች አንዱ የሆነው ሕጻጽ ይዘጋል በሚልም ብዙዎች ጭንቅ ላይ እንደሆኑ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስደተኞች ገልፀዋል።
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት፤ በየዓመቱ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የሚመድበው በጀት በሁለት ሚሊዮን ዶላር እንደቀነሰና፤ በትግራይ ለሚገኙ ስደተኞች የሚውል የዚህ ዓመት በጀት በ34 ሚሊዮን ብር በመቀነሱ፤ ስደተኞቹን ወደ ሌሎቹ ካምፖች ማሸጋሸግ አስፈላጊ እንደሆነ ስሙን እንዲገለጽ ያልፈቀደ የትግራይ ክልል የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ሠራተኛ ይናገራል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የስደተኞች ማሸጋሸግ ሥራ ባለፈው ወር እንደሚያከናውን ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ቢያሳውቅም፤ በአገሪቱ ኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ከተገኘ በኋላ እንደተራዘመና ማዟዟሩ በሚያዚያ ወር መጨረሻ እንደሚጀመር የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ እዮብ አወቀ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) ተወካይ የሆኑት አን ኤኖክተር፤ ተቋሙ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው እርዳታ በ14 በመቶ መቀነሱን አረጋግጠው፤ ይህ ግን ካምፑን ለመዝጋት በቂ ምክንያት እንዳልሆነ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

በዚህ ወቅት ስደተኞቹን ወደ ሌላ መጠለያ ጣቢያ ማዟዟር ለኮሮናቫይረስ እንደሚያጋልጣቸው በመግለጽ፤ ሌሎቹ የስደተኞች መጠለያዎችም በውሃና የህክምና አገልግሎት ችግር ላይ እንዳሉ ጠቅሰዋል።
ቢቢሲ ያነጋገረው የትግራይ ክልል ስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ሠራተኛ ግን ስደተኞች የሚገኙባቸው የዓዲ ሓርሽና ማይ ዓይኒ መጠለያ ጣቢያዎች የኤሌክትሪክና የውሃ አገልግሎት በማግኘት ሕጻጽ ከተባለው ካምፕ የተሻሉ መሆናቸው ይገልጻል።
በኢትዮጵያ የስደተኞች ጉዳይ የሚከታተለው አካል አዲስ የሚገቡ ስደተኞችን መመዝገብ ስላቆመ፤ ሳይመዘገቡ በተለያዩ አካባቢዎች ወድቀው የሚገኙት ስደተኞች ደግሞ፤ የክልሉ ሕዝብ እና አንዳንድ ኤርትራውያን በሚሰጧቸው ጊዜያዊ እርዳታዎች የዕለት ኑሯቸውን እንደሚገፉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
እነዚህ ስደተኞች በቀይ መስቀልና የትግራይ ክልል መንግሥት እርዳታ እየተደረገላቸው ቢሆንም፤ ከባድ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ፣ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ እቃዎች ለመለገስ ወደ ስፍራው የሄዱ በመቀለ የሚኖሩ ኤርትራውያን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ገብረመድኅን በበኩላቸው፤ የፌደራል መንግሥት አዲስ የሚገቡ ስደተኞች የማይቀበላቸው ከሆነ፤ የትግራይ መንግሥት የመኖሪያ ፍቃድ ሰጥቶ በፈለጉት አካባቢ ሄደው እንዲኖሩ ለመፍቀድ እንደሚገደድ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በሽረ ከተማ ብቻ 2 ሺህ ኤርትራውያን ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ተሰጥቷቸው በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሚገኙ አቶ ተክላይ ይናገራሉ።
ሂዩውመን ራይትስ ዋች ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ ስደተኞችን አልቀበልም ማለቱ "ኢሰብአዊና ዓለም አቀፋዊ ሕጎችን የሚጥስ" በመሆኑ፤ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙት የስደተኞች መጠለያ ማዕከላት ውስጥ 80 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት አቶ ተክላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።













