ትግራይ ፡ እጃቸውን ለመንግሥት የሰጡት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ማን ናቸው?

ወ/ር ከይርያ ኢብራሒም

የፎቶው ባለመብት, HOUSE OF FEDERATION

የኢትዮጵያ ፌደራል ሠራዊት የትግራይ ክልል ዋና ከተማን ባለፈው ቅዳሜ ከተቆጣጠረ በኋላ እየተፈለጉ ካሉት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ለመንግሥት እጃቸውን መስጠታቸው ተገልጿል።

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ለዓመታት በክልልና በፌደራል በመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩ ሲሆን በመጨረሻም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው አገልግለዋል።

ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ባለፈው ዓመት ሊደረግ የነበረው ምርጫ ወደ ሌላ ጊዜ በመሸጋገሩ ሳቢያ፤ በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ በነበረው በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል ተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ ወደ ትግራይ በመመለስ ባለፈው ዓመት ሠኔ ወር መጀመሪያ ላይ ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ይታወሳል።

በወቅቱ ምርጫ ማካሄድ አለመቻሉና የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ያስችላሉ የተባሉ አማራጮችን ለመፈለግ የተደረገውን እንቅስቃሴ የተቃወሙት ወይዘሮ ኬሪያ በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ላይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር ስልጣን የለቀቁት።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም በወቅቱ "ሕገ መንግሥት ከሚፈቅደው ውጪ አምባገነናዊ መንግሥት ሲመሰረት ተባባሪ ላለመሆን እና ሕገ መንግሥት በየቀኑ ከሚጥስና አምባገነንነትን ከሚያራምድ ቡድን ጋር ለመስራት ፈቃደኛ ስላልሆንኩ ነው" በሚል በገዛ ፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታውቀው ነበር።

ወይዘሮ ኬሪያ የፌደራል መንግሥት ኃላፊነታቸውን ለቀው ወደ ትግራይ ከተመለሱ በኋላ የፌዴሬሽን ምክር ቤት "ሕገወጥና ተፈጻሚነት የሌለው" ባለው በትግራይ ክልል በተናጠል በተካሄደው ክልላዊ ምርጫ ላይ ተሳትፈው ለክልሉ ምክር ቤት አባልነት መመረጣቸው ተነግሯል።

ወይዘሮ ኬሪያ ከሳምንታት በፊት መንግሥት ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀምና በአገር ክህደት ወንጀል የመያዣ ትዕዛዝ ካወጣባቸው 96 ግለሰቦች መካከል አንዷ ናቸው።

ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም ማን ናቸው?

በኤርትራዋ መዲና በአሥመራ ከተማ የተወለዱት ወይዘሮ ኬሪያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኢንቫይሮታል አንትሮፖሎጂ ማግኘታቸው ይነገራል።

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በትግራይና በፌደራል መንግሥቱ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ በነበረው የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ መግባት ከቻሉ ጥቂት ሴቶች አንዷ ናቸው።

ወይዘሮ ኬሪያ የአገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካላት ከሁኑት ሁለት ምክር ቤቶች የላይኛው ምክር ቤት የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ በመሆን ከሁለት ዓመታት በላይ የሰሩ ሲሆን፤ በዚህ የኃላፊነት ደረጃም ሁለተኛዋ ሴት ነበሩ።

ወይዘሮ ኬሪያ ወደ ከፍተኛው የፌደራል መንግሥቱ የስልጣን ቦታ ከመምጣታቸው በፊት ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ክልል ከወረዳ አንስቶ ባሉ የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ሰርተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትን አፈጉባኤ ከመሆናቸው በፊት በዋናነት በትግራይ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም በትግራይ የደቡብ ምሥራቅ ዞና የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

መነሻ

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመግባባት ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ መካረሩ ይታወሳል።

ተከትሎም የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ባለመቀበል ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደው የተናጠል ምርጫ የፌደራል መንግሥቱን ተቀባይነት ካለማግኘቱ በተጨማሪ በአገሪቱ ምክር ቤቶች ሕገ ወጥ ተብሎ ውድቅ ተደርጓል።

የክልሉ ባለስልጣናትም በበኩላቸው ፌደራል መንግሥቱ በኮቪድ ሰበብ ምርጫን ማራዘሙ "ሕገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ ነው ስልጣኑን አራዝሟል" በማለት የፌደራሉን መንግሥት "ሕገወጥ" ብለው እውቅና መንፈጋቸው አይዘነጋም።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የክልሉን አስተዳዳሪዎች ሕገ መንግሥቱን በመጣስና ከሕግ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል በማለት የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል ክልል አስተዳደር ጋር የነበረውን የቀጥታ ግንኙነት አቋርጦ የበጀት ዕቀባ ጥሎ ነበር።

አለመግባባቱና መካሰሱ ያለማቋረጥ በቀጠለበት ሁኔታ ጥቅም 24/2013 ዓ.ም ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ክልል በነበረው የፌደራሉ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ካደረጉ በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት በትግራይ ክልል ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል።

መንግሥት "ሕግ የማስከበር" ባለውና ከሦሰት ሳምንታት በላይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ሰር ከዋለች በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አሳውቀዋል።