ትግራይ ፡ ሽረን ለመያዝ የተካሄደው ዘመቻና አሁን ያለችበት ሁኔታ በነዋሪዎች ዓይን

የትግራይ ካርታ

መንግሥት ሕግ ማስከበር ያለውና ለሦስት ሳምንታት በዘለቀው ዘመቻ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ከክልሉ ዋና ከተማ ቀደም ብሎ ከተያዙት ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው ሽረ ስለነበረው ሁኔታ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጠይቀናል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሽረ ከተማን ለመቆጣጠር ለህወሓት ታማኝ ከሆኑት ታዋጊዎች ጋር ከፍተኛ የተኩስ ለውጥ አድርገው እንደነበረ የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በምዕራብ ትግራይ የምትገኘው ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በ300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሽረ ከተማ ወደ 80 ሺህ የሚደርስ ሕዝብ መኖሪያ ስትሆን ሠራዊቱ የሽረ ከተማን ከትግራይ ኃይሎች መቆጣጠሩን ይፋ ያደረገው ኅዳር 8/2013 ዓ.ም ነበር።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የተከተማዋ ነዋሪ እንዱለት በሽረ ከተማን ጦርነት የተጀመረው ማክሰኞ ንጋት ኅዳር 8/2013 ዓ.ም ላይ ነበር።

እኚህ የዓይን እማኝ እንደሚሉት ሽረ ከተማ በነበረው ወታደራዊ ግጭት ከባድ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለው ነበር። ነዋሪዎቹም ግጭቱን በመሸሽ ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው ቤተ-ክርስቲያን ተጠልለው እንደነበር ተናግረዋል።

"አብዛኛው ተተኳሾች ያረፉት አጉአዱ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች በቅርብ ወደሚገኘው ቅዱስ አቡነአረጋዊ ቤተክርስቲያን ሸሽተው ነበር" ሲሉ እኚሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ ጠቅሰዋል።

ሽረ ከተማን ለመያዝ በተደረገው ውጊያ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውንም የዓይን እማኙ ተናግረዋል።

"ቢያንስ እኔ በግሌ የማውቃቸው 10 ሰዎች ተጎድተዋል" ብለዋል የዓይን እማኙ። እንደ የዓይን እማኙ ገለጸ ከሆነ አሳቸው ከሚያቋቸው መካከል 6 ሰዎች ተገድለዋል።

አሁንም ቢሆን የሽረ ከተማ ነዋሪዎች ድንጋጤ እና ፍርሃት ውስጥ እንደሚገኙ የዓይን እማኙ ገልጸዋል።

ከተማዋን ለመያዝ የተካሄደው ጦርነት ለስድስት ሰዓታት መዝለቁን እና እኩለ ቀን አከባቢ የአገር መከላከያ ሠራዊት ታንኮች ወደ ከተማ መሃል መግባታቸውን የዓይን እማኙ ተናግረዋል።

በጦርነቱ በከተማዋ የሚገኘ ባለ ሦስት ኮከብ የሆነው ደጀና ሆቴል ጉዳት እንደደረሰበት ነዋሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለቢቢሲ የተላኩ ምስሎችም በሆቴሉ ላይ የደረሰውን ጉዳት ያሳያሉ።

የሆቴሉ ባለቤት የቀድሞ የህወሓት ታጋይ የኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳይ ናቸው። ኮሎኔል ተወልደ ለሁለት ዓመታት ስለተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጽሐፍ መጻፋቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ጊዜ ከተማዋን ተቆጣጥሮ የሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ነዋሪዎች ወደ ቀደሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ለነዋሪዎች መልዕክት እያስተላለፈ መሆኑንም የዓይን እማኙ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ የሕክምና መስጫ ማዕከላት ዝግ እንደሆኑ ሲሆን ግጭቱን በመሸሽ ከከተማዋ የወጡ ነዋሪዎች እስካሁን አልተመሱም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በከተማዋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን በቦታው የሚገኘውን የሰላም ሚኒስቴር የሰላምና ሰብዓዊ ድጋፍ ቡድን አባላት ጠቅሶ ፋና ትናንት ዘግቧል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ዕዝ የምዕራብ ግንባር የሎጅስቲክስ ኃላፊ ጄኔራል ብርሀኑ ጥላሁን እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ በሽረ ከተማ ያለው እንቅስቃሴ ሰላማዊ መሆኑንና ማኅበረሰቡም ያለስጋት የዕለት ተዕለት ተግባሩን እያከናወነ ነው ማለታቸውን ፋና አስነብቧል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት በሽረ እንዳስላሴ ከተማ ተገኝተው ለከተማዋ አዲስ ከንቲባ እንዲሾም መደረጉ ይታወሳል።

ሙሉ ነጋ በወቅቱ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት የከተማዋ ነዋሪዎች የቴሌኮም፣ የመብራት እንዲሁም የውሃ አገልግሎቶች እንዲመለሱላቸው እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀመር ጠይቀው ነበር።