ትግራይ፡ የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ የሕግ የበላይነትን መመለስ አስፈላጊ ነው አለ

በትግራይ ክልል የሕግ የበላይነትን በአፋጣኝ መመለስ አስፈላጊ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ገለጹ።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዳሉት መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ "የሰብአዊ መብቶችን ባከበረ ሁኔታ በአፋጣኝ የሕግ የበላይነትን በፍጥነት መመለስ ያስፈልጋል" ብለዋል።
ዋና ጸሐፊው በሰጡት አጭር መግለጫ ላይ ጨምረው እንዳሉት በክልሉ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በህወሓት ኃይሎች መካከል ውጊያ ከተካሄደ ከአራት ሳምንታት በኋላ "ያለው ወቅታዊው ሁኔታ በጣም አሳስቦኛል" ብለዋል
ግጭቱን ተከትሎ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን የገቡ ሲሆን ሌሎች በርካቶች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሸሽተዋል ተብሏል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ጭምር ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሠብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ ለዚህም ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "ነጻ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር" እንዲመቻች ጠይቀዋል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ለእርዳታ አቅርቦት ሠራተኞች የሚያገለግል መተላለፊያ መስመር እንደሚከፍቱ አስታውቀው ነበር።
በአብዛኛው የትግራይ ክልል ውስጥ ለሳምንታት ተቋርጦ በቆየው የኮምዩኒኬሽን መስመር ምክንያት ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎችን ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኗል።
የትግራይ ክልልን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቅርቡ እንደተናገሩት የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ውስጥ "ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር" እንዲሁም የህወሓት መሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሰራ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድጋሚ ከህወሓት አመራሮች ጋር የሚደረግ ማንኛውም አይነት ድርድር እንደማይቀበሉት አሳውቀዋል።
ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ በተጨማሪ የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ተወካይ ጆሴፍ ቦረል ፎንቴሌስም መንግሥት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር እንዲከፍት ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት "ሕግ ማስከበር" ያለውና ከሦስት ሳምንታት በላይ የቆየው ወታደራዊ ዘመቻ የክልሉ ዋና ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ እንዳበቃ ቢገልጽም የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን በመድረስ እርዳታ ለማቅረብ እንዳልቻሉ እየተናገሩ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ የፌደራል መንግሥቱ ቀዳሚ ትኩረት እንደሚሆን አመልክቶ፤ ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ጋር በመሆን በግጭቱ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ዜጎችንና በትግራይ ክልለ ውስጥ ባሉ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሚገኙትን ስደተኞች ጭምር ለመርዳት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባት ወደ ወታደራዊ ግጭት ከተሸጋገረ በኋላ ግጭቱን በመሸሽ ከቀያቸው የሸሹና በአስር ሺዎች ወደ ጎረቤት አገር መሰደዳቸው የተነገረ ሲሆን በክልሉ ውስጥ ሆነው የሰብአዊ እርዳታ የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ የእርዳታ ድርጅቶች ገልጸዋል።
















