ትግራይ፡ ሁለት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው ትግራይ ውስጥ መገደላቸውን ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, DRC
ሁለት ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ሠራተኞቻቸው መገደላቸውን ገለጹ።
ዳኒሽ ሪፊውጂ ካውንስል እና ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ (አይአርሲ) ድርጅቶች ናቸው በትግራይ ክልል ውስጥ ባልደረቦቻቸው መገደላቸውን ይፋ ያደረጉት።
ዳኒሽ ሪፊውጂ ካውንስል ባሳለፍነው ወር ሦስት የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞቹ መገደላቸውን ሲያስታውቅ፤ ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ (አይአርሲ) በበኩሉ በሽሬ ከተማ ህጻጽ የሰደተኞች መጠለያ ካምፕ ይሰራ የነበረ ባልደረባው መገደሉን አስታውቋል።
ዳኒሽ ሪፊውጂ ካውንስል የተገደሉት በትግራይ ካሉት ፕሮጀክት ጣቢያዎች በአንደኛው ቦታ በጥበቃ ሥራ የተሰማሩት ናቸው ብሏል።
ካውንስሉ በአከባቢው የቴሌኮም አገልግሎት ባለመኖሩ እንዲሁም ወደ ስፍራው ለመጓዝ የደኅንነት ስጋት በመኖሩ የሟች ቤተሰቦችን ማግኘት እና ድጋፍ ማድረግ አለመቻሉን አስታውቋል።
አይአርሲ በበኩሉ በሠራተኛው የተገደለው ኅዳር 10 መሆኑን አረጋግጦ፤ በሠራተኛው መገደል የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን የገለጸ ሲሆን የተገደለው ሠራተኛ ማንነትን ግን ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
አይአርሲ በአከባቢው የቴሌኮም አገልግሎት በመቋረጡ፤ የሠራተኛውን የአሟሟቱን ሁኔታ በተመለከተ ዝርዝር ሁኔታ ማጣራት ለማድረግ አለመቻሉን አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም ሮይተርስ የዜና ወኪል የዲፕሎማቲክና የሰብአዊ እርዳታ ድርጅት ምንጮችን ጠቅሶ፤ በሁለት የተለያዩ የውጪ የተራድኦ ድርጅቶች ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ አራት የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኞች በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ተገድለዋል ሲል ዘግቦ ነበር።
ሮይተርስ በዘገባው በየትኛው አካል ሠራተኞች እንደተገደሉ ያለው ነገር የለም።
ከአንድ ሳምንት በፊት ስለጉዳዩ የሚያውቁት እንደለ በቢቢሲ የተጠየቁት የዲሞክራሲ ግንባታ ሚንሰትር ዛዲግ አብረሃ፤ "አሁን ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም። ገና መረጃው እየተጠራ ነው ያለው። የስልክ አገልግሎትን እየመለስን፣ መንገዶችን እያስተካከልን ነው ያለነው" የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር።
ኢንርናሽል ሬስኪው ኮሚቴ በመላው ዓለም የሰብዓዊ ቀውስ በሚከሰትባቸው ስፍራዎች ሰዎች የጤና፣ የትምህርት አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ የሚሰራ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ደርጅት ነው።
በተያያዘ ከቀናት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ትግራይ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች የፍተሻ ጣቢያ በጣሱ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ላይ እንደተኮሱና በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር።
የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ባለፈው ሳምንት እሁድ ኅዳር 27/2013 ዓ.ም የኤርትራ ስደተኞች የሚገኙበትን ማዕከልን ለመጎብኘት ሲያቀኑ የነበሩና ፍተሻ ጣቢያዎችን ጥሰው አልፈዋል ተብሏል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት የድርጅቱ ሠራተኞ ወዳልተፈቀደላቸው አካባቢ በመግባት የመንግሥትን መመሪያ በመተለለፋቸው ነው የተተኮሰባቸውና የተያዙት።
በፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ችግር ላይ መውደቃቸው የተነገረ ሲሆን በክልሉ ያለው ሁኔታ እንቅስቃሴያቸው ላይ የእራሱ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ሲገልጹ ቆይተዋል።
የሰብአዊ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች በተጨማሪ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢም እንደሆነም እየተገለፀ ነው።
በትግራይ ክልል የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃቱ በመንግሥት ከተገለጸ በኋላ ሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች ወደ ክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ድጋፍ እንዲያቀርቡ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ስምምነት መደረሱ ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ታህሳስ 02/2013 ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል የሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች አስተማማኛና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ለዚህም አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ቁርተኛ መሆኑን ገልጿል።
ጨምሮም ቀደም ሲል ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመሮች እንደሚመቻቹ አመልክቷል።














