በረራ እንዳያደርጉ ተከልክለው የነበሩ ሙስሊሞች ኤፍቢአይን እንዲከሱ ተፈቀደላቸው

አዎሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በፌደራል ወንጀል ምርመራ መስሪያ ቤት (ኤፍቢአይ) በረራ እንዳያደርጉ ስማቸውን በጥቁር መዝገብ ላይ ተመዝግቦ የቆዩት ሦስት ሙስሊም ወንዶች ኤፍቢአይን እንዲከሱ የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በየነላቸው።

ፍርድ ቤቱ እንዳለው በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑት ሦስቱ ግለሰቦች በአገሪቱ ሕግ መሠረት ካሳ መጠየቅም ይችላሉ።

ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን ያቀረቀቡት ግለሶች በኤፍቢአይ አደገኛ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ሥራቸውን እንዳሳጣቸው እና ከሐይማኖታቸው በሚጻረር መልኩ ሌሎች ሙስሊሞች ላይ እንዲሰልሉ ጫና እንደተደረገባቸው ገልጸዋል።

ጠበቆቻቸው እንደሚሉት ማናቸውም ከዚህ በፊት በወንጀል ተጠርጥረው የማያውቁ ሰዎች ናቸው።

ከሦስቱ ሙስሊሞች መካከል አንደኛው በኤፍቢአይ ምክንያት በጠና የታመሙ እናቱን እንኳን ማስታመም እንዳልቻለ የገለጸ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ባለቤቱን ለረጅም ጊዜ ሳያጋኝ መቆየቱን ገልጿል።

ኤፍቢአይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይህንን ተግባር ፈጽመዋል የተባሉት ኤጀንቶቹ ምንም አይነት ክስ እንዳይቀርብባቸው ማድረግ ይችላል።

'ኳሊፋይድ ኢምዩኒቲ' በሚሰኘው የአሜሪካ ሕግ መሠረት የፌደራል ደህንነት ሰራተኞች ሕገ መንግስቱን ቢጥሱ እንኳን ክስ እንዳይቀርብባቸው የሚመከላከል ሲሆን የዴሞክራት ኮንግረስ አባላት ይህ ሕግ እንዲገደብ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ነበር። ነገር ግን ሕጉ በሪፐብሊካኖች ድጋፍ አለው።

''በአሁኑ ሰዓት ጣም ደስ ብሎኛል። ሁሉም ምስጋና ለአላህ ይሁን'' ብሏል በኤፍቢአይ ኢላማ ተደርገው ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው ናቪድ ሺንዋሪ።

''ይህ ድምጻቸው ለማይሰማ ሙስሊሞች ትልቅ ድል ነው'' ሲል ለኤንፒአር ተናግሯል። አክሎም ''ይህ ውሳኔ ለኤፍቢአይና ሌሎች ተቋማት እንደፈቀዱ የሰዎችን ሕይወት ማክበድ እንደማይችሉ ትልቅ መልዕክት ይመስለኛል'' ማለቱ ተገልጿል።

በአሜሪካ በአውሮፕላን መብረር የማይፈቀድላቸው 80 ሺ ሰዎች የሚገኙ ሲሆን ሁሉም የአሜሪካ ዜጎች ባለመሆናቸው ምክንያት ኤፍቢአይን መክሰስ እንደማይችሉ የሶስቱ ሙስሊሞች ጠበቆች ተናግረዋል።