ቴክኖሎጂ ፡ የጉግል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ትምኒት ገብሩን ይቅርታ ጠየቁ

ትምኒት ገብሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትምኒት ገብሩ

የጉግል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሱንድራ ፒቻኢ ትምኒት ከሥራዋ የለቀቀችበትን ሁኔታ በማስመልከት ይቅርታ ጠይቀዋል።

ይሁን እንጂ የጎግል አለቃው ትምኒት እንዴት ልትባረር እንደቻለችም ይሁን ከጉግል መባሯሯን አላረጋገጡም።

ባሳለፍነው ሳምንት የአርቴፌሻል ኢንተለጀንስ- ኤኤይ (የሰው ሰራሽ ልህቀት) ተመራማሪ እና በጉግል የኤአይ የሥነ ምግባር ተመራማሪ ቡድን አጋር መሪ የነበረችው ትምኒት፤ ከጎግል መባረሯን አስታውቃ ነበር።

ትምኒት እንዳሳወቀችው ጉግል ከሥራዋ ያባረራት "ድርጅቱ ትኩረት የተነፈጋቸው ድምጾችን ያፍናል" በማለት ለሥራ ባልደረቦቿ የኢሜል መልዕክት ከላከች በኋላ ነው።

ኩባንያው "ከአመራር ውጪ ለሆኑ ተቀጣሪዎች የላክሽው ኢሜል የጉግል አስተዳደር ከሚፈቅደው አሠራር ውጪ ነው" የሚል ኢሜል እንደላከላት ተናግራለች።

በትውልድ ሕንዳዊ የሆኑት የጎግል አለቃ ሱንድራ ፒቻኢ ኩባንያው ትምኒት “ከጉግል የተለየችበትን ሁኔታ መመርመር ይኖርበታል” ብለዋል።

ለጉግል ሠራተኞች በላኩት የኢሜይል መልዕክት ላይ ሱንድራ “ተጽእኖ ፈጣሪ እና ባለ ብዙ ተሰጥኦ ጥቁር ሴት ጉግልን በሃዘን ስለተሰናበተች ኃላፊነት መውሰድ ይኖርብናል” ብለዋል።

ትምኒት በበኩሏ ለሥራ አስፈጻሚው የኢሜል መልዕክት “ይህ ይቅርታ መጠየቅ አይደለም” ስትል ምላሽ ሰጥታለች።

ትምኒት ከጉግል ከመባሯ በፊት ከሌሎች የኩባንያው ተመራማሪዎች ጋር የጻፈችው የጥናት ጽሑፍ እውቅና እንድትነፍግ እና በጥናት ጸሑፉ የተሳተፉ ሰዎችን ስም ዝርዝር ከጥናት ወረቀቱ እንድታነሳ ተነግሯት እንደነበረ ገልጻለች።

በሰው ሠራሽ ልህቀትና ተያያዥ የቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚሠሩ እውቅ ባለሙያዎች የትምኒትን መባረር በመቃወም ትዊተር ላይ ድምጻቸውን ሲያስሙ ቆይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ የጉገል ሠራተኞችን ትምኒት ገብሩን የሚደግፈው ደብዳቤ ላይ በመፈረም ከጓኗ መቆማቸውን ሲገልጹ ነበር።

የትምኒት መባረርንም እንደ ዋሽንግተን ፖስት፣ ብሉምበርግ እና ኒው ዮርክ ታይምስ ያሉት ግዙፍ የአሜሪካ የሚዲያ ተቋማት ይዘውት ወጥተዋል።