ትግራይ፡ የመጀመሪያው የህወሓት ከፍተኛ አመራር ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, ENA
የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሬያቸዋለሁ ካላቸው የህወሓት ከፍተኛ አመራር መካከል አንዱ የሆኑት አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) ሐሙስ ታኅሳስ 01/2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተነገረ።
በዚህም ትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ወታደራዊ ግጭት በኋላ ፍርድ ቤት በመቅረብ ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የመጀመሪያው ሆነዋል።
በትግራይ ክልል እንዲሁም በፌደራል መንግሥቱ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት የአዲስዓለም ባሌማን (ዶ/ር) ጉዳይ የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።
ከአንድ ወር በፊት በትግራይ ውስጥ ወታደራዊ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የእስር ትዕዛዝ ከወጣባቸው የህወሓት አመራሮች መካከል አንዱ የነበሩት አዲስዓለም (ዶ/ር) በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።
ፖሊስ አዲስዓለም ባሌማን (ዶ/ር) የጠረጠረበትን በተለያዩ የተለያዩ ወንጀሎች ያቀረበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈፀምና ከባድ የጦር መሳሪያዎች እንዲዘረፉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እንዲሁም በማይካድራ ንፁሀን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት በማመቻቸት" መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለችሎቱ ማስረዳቱን ፋና ዘግቧል።
ፖሊስ በተጨማሪም አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) ላይ በርከት ያሉ የተለያዩ ክሶችን ያቀረበ ሲሆን ግለሰቡ አምባሳደር በነበሩበት ዘመን አገሪቱ ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት እንዲበላሽና እንዲቋረጥ ተጽዕኖ በማድረግ፣ የመንግሥት መረጃና ምስጢሮችን አሳልፈው በመስጠት እንዲሁም ከኦነግ-ሸኔ አመራሮች ጋር በመገናኘትና የመንግሥትን ምስጢር አሳልፈው እንደሰጡና ከቡድኑ ጋር ሲሰሩ እንደነበር ለችሎቱ ገልጿል።
ተጠርጣሪው አዲስዓለም (ዶ/ር) ከህወሓት አመራሮች ጋር በመተባበር የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም፣ ሁከትና አመጽ እንዲፈጠር የተለያዩ ድርጊቶችን በማስተባበር መጠርጠራቸው ተነግሯል።
የአፍሪካ ሕብረት ባለስልጣናትን በመቅረብ በመንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ግፊት በማድረግ እንዲሁም ከአንድ የቻይና አምባሳደር ጋር በመገናኘት የቻይና እና የህወሓት ኮሙኒስት ፓርቲ እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሲጥሩ እንደነበርም ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ መግለጹ ተነግሯል።
ተጠርጣሪው አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) በበኩላቸው የተባሉትን ወንጀሎች አለመፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናገረው "ሰኞ ዕለት ከደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር በሽምግልና ጉዳይ ስነጋገር ቆይቼ ረቡዕ በቁጥጥር ስር ውያለሁ" በማለት ከሌሎች አምባሳደሮችንና ባለስልጣናት ጋር የተነጋገሩትም በሽምግልና ጉዳይ ላይ እንደሆነ መግለፃቸውን የፋና ዘገባ አስነብቧል።
ፖሊስ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው የሚያስረዱ በቂ መረጃዎች እንዳሉት ገልጾ፤ ምርመራውን ለማካሄድ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱንም የፖሊስን ጥያቄ ተቀብሎ ፈቅዷል።
በተመሳሳይም ለረጅም ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት የአምባሳደር ስዩም ባለቤትና ልጃቸው በፖሊስ ተይዘው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተገልጿል።
ሐሙስ ፍርድ ቤት የቀረቡት የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት የስዩም መስፍን ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ ፈለገህይወት በርሔና ልጃቸው አጋዚ ስዩም ሲሆኑ፤ ፖሊስም በተለያዩ የወልጀል ድርጊቶች ጠርጥሮ በቁጥጥር ሰር እንዳዋላቸው ለፍርድ ቤት ገልጿል።
ፖሊስ የጀመረውን ምርመራ ለማካሄድ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ስምንት ቀናት እንደተፈቀደለት ፋና ዘግቧል።
የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው ህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታደራዊ ግጭት መሸጋገሩን ተከትሎ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች እንደሚፈለጉ በተገለጹ የቡድኑ አመራሮች ላይ ፖሊስ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።
ለወታደራዊው ግጭት ምክንያት ከሆነው በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ጨምሮ በበርካታ ከፍተኛ ወንጀሎች ጠርጥሮ መንግሥት እፈልጋቸዋለሁ ካላቸው የህወሓት አመራሮች በተጨማሪ በከፍተኛ ወታደራዊና የፖሊስ መኮንኖችም ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።
አስካሁን በቁጥጥሩ ስር እንደዋሉ በይፋ የተገለጹት ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና አምባሳደር የነበሩት አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) እንዲሁም የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ናቸው።














