ትግራይ፡ በህወሓት ኃይሎች ታግተው የነበሩ 1 ሺህ መኮንኖች መለቀቃቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Eth News Agency
በህወሓት ኃይሎች ታግተው የነበሩ ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ዕዝ መስመራዊና ከፍተኛ መኮንኖች መለቀቃቸውን የአገር መከላከያ አስታወቀ።
በህወሓት ኃይሎች ታግተው ከነበሩት እና ከተለቀቁት መካከል የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዲየር ጀነራል አዳምነህ መንግስቴ እንደሚገኙበት ኢዜአ የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማን ጠቅሶ ዘግቧል።
የአገር መከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ ባደረጉት የጋራ ኦፕሬሽን የተለቀቁት 1 ሺህ ያክሉ የጦር አባላት የመስመራዊና ከፍተኛ መኮንኖች ናቸው ተብሏል።
ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአገር መከላከያ አባላቱ ጥቅምት 24 ቀን ምሽት ላይ የእራት ግብዣ ተብለው ከተጠሩ በኋላ ታፍነው የተወሰዱ ናቸው።
የህወሓት ኃይሎች በሸሹባቸው ቦታ ሁሉ በቁጥጥራቸው ሥር ይገኙ የነበሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላቱን ይዘው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ተገልጿል።
የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ባደረጉት ኦፕሬሽን መስመራዊና ከፍተኛ መኮንኖቹ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከህወሓት ኃይሎች መለቀቃቸውን ሜጀር ጀነራል መሐመድ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ሜ/ጀ መሐመድ የህወሓት አባላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ጨምረው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በትግራይ ልዩ ኃይል ተይዘው ከነበሩት መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከቀናት በፊት ተለቀው ወደ አማራ ክልል መግባታቸው ይታወሳል።
ከእነዚህ መካከል በዋግ ኽምራ በኩል የተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅን ተሻግረው ሰቆጣ ከገቡትን የሠራዊቱን አባላት መካከል ቢቢሲ የተወሰኑትን አነጋግሮ ነበር።
የ31ኛ አድዋ ክፍለ ጦር ውስጥ የክፍለ ጦር አባል የሆነው አምሳ አለቃ አብርሐም ባየ 22 ቀናትን በትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ቁጥጥር ስር ቆይቶ ነበር።
አምሳ አለቃ አብረሐም በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በነበሩበት ወቅት ወደተለያዩ ስፍራዎች ይዘዋቸው ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ምርኮኛ ሆነው በቆዩባቸው ቀናትም በሚሊሻ እና በማረሚያ ቤት ጠባቂዎች ሲጠበቁ መቆየታቸውን የሚናገረው አምሳ አለቃ አብርሃም፣ "ምንም አይነት ንግግር አልነበረንም። በተለይ አብይ አዲ በነበርንበት ወቅት ሚሳኤሎች ሲተኮሱ በቦታው ሆነን እየተመለከትን ነበር። ከባድ መሳሪያዎች ወደ ስፍራው ሲጓጓዙ ስንመለከት በቀሪው የአገራችን ክፍል ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ስለማናውቅ በጣም ጭንቀት ውስጥ ነበርን፤ እንቅልፍም አልነበርንም" በማለት የነበራቸውን ቆይታ ገልጿል።
ሌላኛው የሠራዊቱ አባል አስር አለቃ ኢብራሂም ሃሰን በተመሳሳይ ምርኮኛ ሆነው በቆዩባቸው ጊዜያት የህወሓት ኃይሎች ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቅሷቸው እንደነበረ ያስታውሳል።
ኢብራሂም ተይዘው የቆዩባቸው ቀናት እጅግ አስቸጋሪ እንደነበሩ በመግለጽ ይራቡ እንደነበረም ያስታውሳል "ጠዋት አንድ ዳቦ ይመጣል። ለምሳም አንድ ዳቦ ነው የሚሰጠን። አንዳንዴ ጠዋት ከበላን ምሳ ላይሰጠን ይችላል" ሲል ተናግሯል።
የህወሓት ኃይሎች ይዘዋቸው ከነበሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ከ1ሺህ 200 በላይ ተለቀው ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ በላይ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው አለመግባባት ተካሮ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።
መንግሥት "ሕግ የማስከበር" ባለውና ከአንድ ወር በላይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደዋል።
የትግራይ መዲና የሆነችው መቀለ በፌደራል መንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተናግረው ነበር።













