ኮሮናቫይረስ፡ ሀብታም አገራት ክትባት ያላግባብ እያከማቹ መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሀብታም አገራት ያላግባብ የኮሮናቫይረስ ክትባት እያከማቹ እንደሆነና ይህም ድሀ አገራት ክትባቱን የሚያገኙበትን እድል እንደሚያጠበው ተገለጸ።
ለክትባት ፍትሐዊ ስርጭት የቆመው "ዘ ፒፕልስ ቫክሲን አልያንስ" የተባለው ስብስብ እንዳለው፤ ወደ 70 የሚጠጉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራች ከአስር ዜጎቻቸው ለአንድ ሰው ብቻ ነው ክትባት መስጠት የሚችሉት።
ኦክስፎርድ እና አስትራዜንካ በጥምረት ከሚሠሩት ክትባት 64 በመቶውን በታዳጊ አገራት እንደሚያከፋፍሉ አስታውቀዋል።
ክትባቱ በፍትሐዊ መንገድ ለመላው ዓለም እንዲከፋፈል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው።
ኮቫክስ የተባለው ጥምረት 700 ጠብታ ለ92 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ለማከፋፈል ተስማምቷል።
"ዘ ፒፕልስ ቫክሲን አልያንስ" ውስጥ አምንስቲ፣ ኦክስፋምና ሌሎችም የመብት ተሟጋቾች ይገኙበታል።
ይህ ስብስብ እንዳለው፤ ከሆነ በቂ ክትባት ባለመኖሩ መድኃኒት አምራቾች በርካታ ክትባት እንዲመረት የቴክኖሎጂ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ሁሉም ክትባቶች ፍቃድ ካገኙ፤ ሀብታም አገራች ለመላው ዜጎቻቸው ከሚበቃው ሦስት እጥፍ ጠብታ ለመግዛት ከወዲሁ መስማማታቸው ተጠቁሟል።
ለምሳሌ ካናዳ ለእያንዳንዱ ዜጋዋ አምስት እጥፍ ክትባት ለማግኘት አስቀድማ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።
ሀብታም አገራች ከመላው ዓለም 14% ብቻ ቢሆኑም 53% ክትባት ገዝተዋል።
የኦክስፋም የጤና ፖሊሲ ኃላፊ አና ማርዮት "ማንም ሰው ሕይወቱን የሚያተርፍ ክትባት ሊከለከል አይገባም። ክትባት ማግኘት እና አለማግኘት በአገር የገንዘብ አቅም መወሰን የለበትም" ብለዋል።
አሁን ያለው ሁኔታ ካልተለወጠ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የኮቪድ-19 ክትባት ላያገኙ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
"ዘ ፒፕልስ ቫክሲን አልያንስ" ሁሉም መድኃኒት አምራቾች የኮቪድ-19 ክትባት ሂደትና ቴክኖሎጂውን በማጋራት ጠብታው በቢሊዮኖች እንዲመረት ጥሪ አቅርቧል።
የዓለም ጤና ድርጅት የመረጃ ልውውጡን ማሳለጥ እንደሚችልም ተጠቁሟል።
አስትራዜኒካ ለታዳጊ አገራት ከክፍያ ነጻ ክትባቱን እንደሚያቀርብ አስታውቋል። የአስትራዜኒካ ክትባት ከሌሎቹ ርካሽ ነው። ማቀዝቀዣ ውስጥ ለማስቀመጥ ምቹ ስለሆነም በቀላሉ ማከፋፈል ይቻላል።
ሆኖም ግን አንድ ተቋም ብቻውን ለመላው ዓለም ክትባት ማዳረስ እንደማይችል የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
የፋይዘር እና ባዮንቴክ ክትባት በዩናይትድ ኪንግደም ፍቃድ አግኝቷል። ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እየተሰጠም ነው።
ክትባቱ በቅርቡ በአሜሪካ እና የአውሮፓ አገሮች ፍቃድ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ማለት ደግሞ ለድሀ አገራት እስኪከፋፈል ጊዜ ሊወስድ ይችላል ማለት ነው።
በተጨማሪም የሩስያው ክትባት (ስፑትኒክ) ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገቡ ተገልጿል። ሌሎች አራት ክትባቶች የመጨረሻ የሙከራ ደረጃ ላይ እንደደረሱም ተዘግቧል።












