የኮቪድ-19 መረጃን የሚያጠናቅሩት አሜሪካዊቷ ተመራማሪ ቤታቸው በፖሊስ ተፈተሸ

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images
በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት የኮቪድ-19 መረጃዎችን የማጠናቀር ኃላፊነት የነበራቸው ተመራማሪ ሬቤካ ጆንስ መኖሪያ ቤት በፖሊስ መፈተሹ ተሰምቷል።
ተመራማሪዋ በአሜሪካ የጤና ዲፓርትመንት በቀረበባቸው ክስ መሰረት ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ተጥሎ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለማላላት በማሰብ ስለቫይረሱ የተሰበሰቡ መረጃዎችን ሆን ብለው አስተካክለዋል።
ኃላፊዋ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስቀመጧቸው ተከታታይ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ቤታቸውን ሲፈትሹ ታይቷል።
በተጨማሪም ፖሊስ የኃላፊዋን ላፕቶፕና ተንቀሳቃሽ ስልቅ በቁጥጥር ስር አውለዋል።
ፖሊስ እንደሚለው ፍተሻውን ለማድረግ የተገደደው የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስርአት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ እንደሆነ ቢገልጽም ኃላፊዋ ግን ምንም የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።
ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ሬቤካ ጆንስ ይሰሩበት የነበረው የአሜሪካ ጤና ዲፓርትመንት ላይ ክስ በማቅረባቸው ምክንያት ከስራቸው ተባረው የነበረ ሲሆን ኃላፊዋ ከዚህ በኋላ በግላቸው የራሳቸውን መረጃ መሰብሰብና ማጠናቀር ጀምረው ነበር።
ፖሊስ እንደሚለው በያዝነው ሕዳር ወር ላይ ለድንገተኛ ምላሽ ክፍል ሰራተኞች ፍቃድ ያላገኘ መልዕክት የተላከ ሲሆን መልዕክቱም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት ሀሳባቸውን እንዲገልጹ የሚጠይቅ ነበር።
የፍሎሪዳ የሕግ ማስከበር ዲፓርትመንት ባወጣው መግለጫ ላይ በመረጃ ስርአቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት መነሻው ከኃላፊዋ መኖሪያ ቤት አድራሻ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ይህንን መሰረት በማድረግም የፍተሻ ፈቃድ እንደተገኘ አስታውቋል።
የዲፓርትመንቱ ኮሚሽነር ሪክ ስዌሪንገን እንዳሉት ኃላፊዋና ልጆቻቸው መሳሪያ ተደግኖባቸው ፍተሻ ተካሂዷል ማለታቸውን በተመለከተ ሐሰት ነው ብለዋል።
''መርማሪዎቹ በተለመደው ሕጋዊ አሰራር መሰረት ፍተሻውን አካሂደዋል፤ በዚሁም ለምርመራው የሚጠቅሙ በርካታ መሳሪያዎችን አግኝተዋል'' ሲሉ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
''በየትኛውም ሁኔታ ምንም አይነት መሳሪያ ማንም ላይ አልተደገነም''.ኃላፊዋ ቤታቸው ከተበረበረ በኋላ ለአንዳንድ ወጪዎች እንዲረዳን በማለት ባዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ ደግሞ በመጀመሪያዎቹ ሰባት ሰአታት ብቻ 65 ሺ ዶላር ማግኘታቸው ተገልጿል።












