የአርጀንቲናዋ ሴናተር የማራዶና ምስል በገንዘብ ኖት ላይ እንዲታተም ጠየቁ

የማራዶና ምስል በገንዘብ ኖት

የፎቶው ባለመብት, AFP

አንዲት አርጀንቲናዊ ሴናተር የእግር ኳስ ኮከቡ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ምስል በአዲስ የገንዘብ ኖቶች ላይ እንዲታተም ሀሳብ ማቅረባቸው ተሰምቷል።

የቀድሞው የአርጀንቲና ኮከብ ተጫዋች እና በኋላም የአገሩ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ያረፈው ቤቱ ውስጥ ሳለ በልብ ችግር እንደሆነ ተገልጿል።

ማራዶና በዚህ ወር መጀመሪያ አካባቢ በአንጎሉ ውስጥ ላጋጠመው የደም መርጋት የተሳካ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለት የነበረ ሲሆን በተከታይነትም ከአልኮል ሱስ ለመላቀቅ ሕክምና ይደረግለታል ተብሎ ነበር።

ሴናተር ኖርማ ዱራናጎ ሰኞ ዕለት ለአገሪቱ ኮንግረስ ሃሳቡን ያቀረቡ ሲሆን በአገሪቱ ትልቁ የሆነው የ1 ሺ ፔሶ (የአርጀንቲና መገበያያ ገንዘብ) ላይ ምስሉ ቢቀረጽ ምን ይመስላችኋል ሲሉ ጠይቀዋል።

ሴናተሯ እንደሚሉት የማራዶና የፊት ምስል በአንድ በኩል በለጀርባው በኩል ደግሞ እግር ኳሰኛው የሚታወቅባቸው ድንቅ ድንቅ ግቦች በምስል እንዲታተሙ ፍላጎት አላቸው።

በዚህም መሰረት በ1 ሺ ፔሶ ላይ የዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ፊት እና በጀርባው ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1986 በሜክሲኮው የዓለም ዋንጫ እንግሊዝ ላይ ያስቆጠራት ሁለተኛ ጎል ሊታተም እንደሚችል 'ላ ናሲዮን' የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።

በተጨማሪም ሴናተሯ የማራዶና ምስል በቴምብሮች ላይም እንዲቀር ሀሳብ አቅርበዋል።

'' ይሄ ሃሳብ እውቁን እግር ኳሰኛ ለማሰብ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም እንደሚኖረው ይገመታል። ጎብኘዒዎች ወደ አርጀንቲና ሲመጡ የማራዶና ምስል ባለበት ኖት መገበያያትና ለማስታወሻ ኖቱን ይዘው መሄድ እንዲመርጡ ያደርጋቸዋል'' ሲሉ አስረድተዋል ሴናተሯ።

የዓለማችን የምንጊዜም ታላላቅ ተጫዋቾች ከሚባሉት አንዱ የሆነው ማራዶና አርጀንቲና እአአ በ1986 የዓለም ዋንጫ ባለቤት ስትሆን የቡድኑ አምበል የነበረ ሲሆን ድንቅ ችሎታውንና የታወቀባቸውን የኳስ ጥበቡን በማሳየት ዓለምን አስደምሞ ነበር።

በተለይ በወቅቱ አርጀንቲና ከእንግሊዝ ጋር ባደረገችው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ እሱ "የእግዜር እጅ" ያላትና ዳኞች ሳያዩ በእጁ ያስቆጠራት ግብ ዘወትር ትታወሳለች።

በተጨማሪም ለስፔኑ ባርሴሎናና ለጣሊያኑ ናፖሊ ቡድኖች በአውሮፓ ውስጥ የተጫወተ ሲሆን፤ በጣሊያን ሴሪ አ ውስጥም ሁለት ጊዜ ዋንጫ ለማንሳት በቅቶ ነበር።

የአርጀንቲና እግር ኳስ ማኅበር የማራዶና ሞት በተሰማ ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጣው መግለጫ "በጀግናችን ሞት በጣሙን አዝነናል" በማለት "ሁልጊዜም በልባችን ውስጥ ትኖራለህ" ብሏል።

ማራዶና ለአገሩ አርጀንቲና በአራት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ በተደረጉ 91 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 34 ግቦችን አስቆጥሯል።