ለጭቁኖች ተቆርቋሪው የክፍለ ዘመኑ ታላቅ የእግር ኳስ ጥበበኛ ዲያጎ ማራዶና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንፀባራቂ ስብዕና፣ ድንቅ ችሎታ፣ የላቀ አእምሮ፣ ተናዳጅ፣ ቁጡ፣ ለተጨቋኞች አዛኝ፣ እብሪተኛ ሌላም ሌላም. . .
በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የእግር ኳሱ ሊቅ ዲያጎ ማራዶና በህይወት እያለ ይሰጠው የነበሩ ስሞች ናቸው - የዓለማችን የእግር ኳስ ጀግና።
ለእግር ኳስ የተፈጠረ ነው የሚባልለት አርጀንቲናዊው ማራዶና ለየት ያለ ድንቅ ችሎታን፣ ራዕይና ፍጥነትን ቀልብ ከመሳብ ጋር በማጣመር በርካታ አድናቂዎቹን አስደምሟል።
"የአምላክ እጅ" ተብሎ በሚጠራው አወዛጋቢ ጎል፣ በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ መዘፈቁና ሌሎች ከግል ህይወቱ ጋር በተያያዘም ደጋፊዎቹ የተመሳቀለ እይታ እንዲኖራቸው አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት ጣልያንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያሉ አድናቂዎቹ እየዘከሩት ሲሆን በተለይም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ ታላቅ ቦታ አለው።
በርካታ ጊዜያትም "ልቤም ሆነ ውስጤ ፍልስጥኤማዊ ነው" ሲል የተሰማው ማራዶና "ጭቆናን እናውቃለን" በማለትም እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ለፍልስጥኤም ያለውን ድጋፍ አሳይቷል።
አጭርና ጣፋጭ ህይወት- የእግር ኳሱ ሊቅ
ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና የተወለደው በአርጀንቲናዋ፣ ቦነስ አይረስ የድሆች መንደር ውስጥ ከዛሬ 60 ዓመት በፊት ነበር። የእግር ኳስ ፍላጎቱም የተጠነሰሰው ገና በታዳጊነቱ ሲሆን፤ በእግር ኳስ ታሪክ ታላቅ ቦታ ላይ መድረስ ችሏል። አንዳንዶችም ከታላቁ የብራዚል እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ያስበልጡታል።
ማራዶና በ491 ጨዋታዎች 259 ጎሎችን በማስቆጠል የደቡብ አሜሪካ ተቀናቃኙን ፔሌን በመብለጥ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ ተጫዋች መሆን ቢችልም፤ ወደ በኋላ እግር ኳስን በበላይነት የሚያስተዳድረው ፊፋ የምርጫ ሕጉን በመቀየሩ ሁለቱም የክፍለ ዘመኑ ምርጥ በመሆን ተሰይመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእናቱ ማህፀን እግር ኳስን የለመደ ይመስል ማራዶና ገና በህፃንነቱ ነበር የላቀ ችሎታውን ማሳየት የጀመረው። ሎስ ሴቦሊታስ የተባለ የታዳጊዎች ቡድንን በመምራት በ136 ጨዋታዎች ባለመሸነፍ አይበገሬነቱን አሳይቷል። የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ህይወቱንም የጀመረው በ16 ዓመቱ አካባቢ ነው።
አጠር ብሎ ደንደን ያለ ሰውነት ያለው ማራዶና ቁመቱም 1.65 ሜትር ነው። ሲታይ የተለመደው አይነት የስፖርተኛ ሰውነት የለውም።
ነገር ግን ቀልጣፋነቱ፣ ነገሮችን ቀድሞ የመረዳት ችሎታው፣ የኳስ ቁጥጥሩ፣ ኳስ ማንቀርቀብና ቶሎ ማሳለፍ መቻሉ ላለመረጋጋቱና ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመውን የክብደት ችግሩን አካክሶለታል።
ምንም እንኳን የተቀናቃኝ ቡድንን ተከላካዮች በቀላሉ ማለፍ ቢችልም ማራዶና በግል ህይወቱ ራሱን በርካታ ጊዜ ችግር ውስጥ ተዘፍቆ አግኘቶታል።
የአምላክ እጅና የክፍለ ዘመኑ ጎል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማራዶ ለአገሩ በተሰለፈባቸው 91 ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ላይ 34 ጎል አስቆጥሯል። ነገር ግን ይህ ምናልባት ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ጨዋታ ታሪኩ ውስጥ ከወንዝ ውሃን በማንኪያ እንደ መጨለፍ የሚቆጠር ነው።
በጎሮጎሳውያኑ በ1986 ሜክሲኮ ላይ በተደረገው የዓለም ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑን የመራው ማራዶና ከአራት ዓመታት በኋላም አገሩን ለመጨረሻ ዙር አደረሳት።
በተለይም በሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ የተከሰተው ውዝግብ የማራዶና መታወቂያ ሆነ።
በወቅቱ አርጀንቲናና እንግሊዝ ያደርጉት ጨዋታ እግር ኳስ ብቻ አልነበረም፤ ፖለቲካም የተቀላቀለበት ነበር።
ከውድድሩ ከዓመታት በፊት ለአስር ሳምንታት ያህል ፎክላንድስ ተብላ በምትጠራው ደሴት ምክንያት አርጀንቲና ከእንግሊዝ ጋር ጦርነት ገጥማ ነበር። በጨዋታው ላይ ሁለቱም የውጊያው መንፈስ ሳይለቃቸው ወደ ሜዳ ገብተው በእግር ኳሱም ላይ ይሄው የፀበኝነት ስሜት ነበር የተንፀባረቀው።
ለ51 ደቂቃዎችም ያህል ያለ ምንም ጎል ጨዋታው ሲካሄድ ቆይቶ በድንገት ማራዶና ከግብ ጠባቂው ፒተር ሺልተን ጋር ዘሎ የተሻማትን ኳሷን በተቃራኒው መረብ አስቆጠረ።
ማራዶና ከጨዋታው በኋላም ግቧ እንዴት እንደተቆጠችረ በተናገረበት ወቅት በጎሉ ውስጥ "ማራዶና ትንሽ ነበረበት፤ የአምላክም እጅ በትንሹ ነበረበት" በማለት ተናገረ።
በዚሁ ጨዋታ ላይ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ብዙዎች 'የክፍለ ዘመኑ ጎል' ብለው የጠሩትን ግብ አስቆጠረ። የተቀናቃኙን ቡድን አባላት እጥፍጥፍ አድርጎ፤ ሜዳው ላይ ብቻውን ያለ ሰው ይመስል፤ ጎሏን አስቆጠረ።
"ድንቅ ጎል ነበረች። የእግር ኳስ እልቅና የታየበት፤ የሚገርም ነው" በማለት የቢቢሲው ዘጋቢ ቤሪ ዴቪስ ተናግሯል።
በጨዋታው እንግሊዝ አንድ ጎል ብታስቆጥርም፤ አርጀንቲና 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች። ለማራዶና ማሸነፉ ከጨዋታው፤ ከእግር ኳስም በላይ ነበር "እንግሊዞችን መዘረር" ፖለቲካዊ ድልም ነበረው።
የናፖሊው ጀግና- በአደንዛዥ እፅ መዘፈቅ
የዓለም አቀፍ የዝውውር ክብረ ወሰንን ማራዶና ሁለት ጊዜ መስበር ችሏል። በአገሩ ሲጫወትበት ከነበረው ቦካ ጁኒየርስ ወደ ስፔኑ ባርሴሎና በጎሮጎሳውያኑ 1982 ሲዛወር በ3 ሚሊዮን ፓውንድ ነበር።
ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ወደ ጣልያኑ ክለብ ናፖሊም በ5 ሚሊዮን ፓውንድ ተዛወረ።
በጣልያኗ ሳን ፓውሎ ስታዲየም በሄሊኮፕተር ሲያርፍም 80 ሺህ አድናቂዎቹና ወዳጆቹ ተገኝተው ነበር- አዲሱን ጀግና ለመቀበል።
ይህም በእግር ኳስ ታሪኩ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበት ወቅት ነው። ክለቡ በ1987 እና በ1990 የሊጉ አሸናፊ እንዲሆን እንዲሁም የአውሮፓ ሊግ ዋንጫን በ1989 እንዲያነሳም ቀዳሚውን ሚና የተጫወተው ማራዶና ነው።
የመጀመሪያውን ድል በማስመልከት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በጎዳናዎች ላይ በመውጣት ለአምስት ቀናት ያህል ደስታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት ማራዶና የሁሉንም ትኩረት ሳበ የሚጠበቅበትም ኃላፊነት ከፍተኛ ሆነ። ይህ ደግሞ ጫናንና መጨናነቅን አስከተለ።
"ታላቅ ከተማ ናት ግን መተንፈስ እንኳን አልቻልኩም። ነፃ ሆኜ በመንገዶች ላይ መረማመድ እፈልጋለሁ። እኔም እንደ ሌላው ሰው ነኝ" ብሏል በወቅቱ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከጣልያኑ የካሞራ ማፊያ ቤተሰብ ጋር ግንኙነት አለው በሚል፣ የኮኬይን አደንዛዥ እፅ ሱስ ውስጥ መዘፈቅና ከልጅ ማደጎ ጋር በተፈጠረ እሰጣገባም ጋር ስሙ በተደጋጋሚ መነሳት ጀመረ።
በጎርጎሳውያኑ በ1990 ጣልያን ላይ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ በጀርመን 1 ለ 0 አገሩ አርጀንቲና መሸነፏን ተከትሎ እንዲሁም በቀጣዩ ዓመትም በተደረገለት ምርመራ አደንዛዥ እፅ መጠቀሙ በመታወቁ ለ15 ወራት እንዲታገድ ምክንያት ሆነ ።
ከዚህ ሁሉ አገግሞና ራሱን አድሶ በጎሮጎሳውያኑ 1994 አሜሪካ ላይ ወደ ተካሄደው የዓለም ዋንጫ ቢመለስም ጎል አስቆጥሮ ደስታውን የገለፀበት መንገድ ያልተለመደና በርካቶችንም ያስደነገጠ ነበር።
ማራዶና የታገደውን ኤፊድሪን የተባለ የተከለከለ አበረታች መድኃኒት ወስዶ በመገኘቱ ከውድድሩ እንዲወጣ ተደረገ።
ህይወት ከጡረታ በኋላ
ለሦስተኛ ጊዜ አበረታች እፅ በደሙ ውስጥ ከሦስት ዓመት በኋላ መገኘቱን ተከትሎ በ37 ዓመቱ ከእግር ኳስ ጨዋታዎች ራሱን አገለለ።
ነገር ግን ተጫዋቹን ችግሮች አልለቀቁትም።
በጋዜጠኞች ላይ ተኩሷል በሚልም ሁለት ዓመት ከአስር ወራት እስር ቢፈረድበትም በማስጠንቀቂያ ታልፏል።
የኮኬይንና የአልኮል መጠጡም የጤና እክል አስከትሎበታል ተብሏል። በከፍተኛ ሁኔታም ኪሎው የጨመረ ሲሆን፤ በአንድ ወቅት 128 ኪሎ ግራምም ይመዝን ነበር። በጎሮጎሳውያኑ 2004 በልብ ህመም ምክንያት ፅኑ የህሙማን ክፍል ውስጥ ገብቶም ነበር።
ማራዶና ክብደቱን ለመቀነስ ቀዶ ህክምና ያደረገ ሲሆን ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስም ለመላቀቅ ኩባ መኖር ጀመረ፤ የቀድሞውን የኩባ መሪና ሶሻሊስትና የነፃነት ታጋይ ፊደል ካስትሮንም አግኝቷቸው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ ሁሉ በኋላ በጎሮጎሳውያኑ 2008 የአርጀንቲና ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣን ሆነ።
በዚያው ዓመትም በነበረው የዓለም ዋንጫ አገሩ ለሩብ ፍፃሜ የበቃች ቢሆንም በጀርመን 4 ለ 0 ከተሸነፈ በኋላ ከቡድኑ ጋር የነበረው የሁለት ዓመት ቆይታ ተቋጫ።
ውሻው ሻሪ ፔይ ከንፈሩን ነክሳው ቀዶ ህክምና ማድረጉ፣ ከትዳሩ ውጭ ለወለደው ለዲያጎ አርማንዶ ጁኒየር እውቅና መስጠቱም ስሙ ከየመድረኩ እንዳይጠፋ አደረገው።
ከሁለት ዓመት በፊት ሩሲያ በተደረገው የዓለም ዋንጫ አርጀንቲናና ናይጄሪያ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ተገኝቶ የነበረው ማራዶና የብዙዎች መነጋገሪያነት ሆኖ ነበር።
ከናይጄሪያ ደጋፊ ጋር አብሮ መደነሱ፣ ከጨዋታው በፊት ወደ ሰማይ አንጋጦ ያደረገው ፀሎት፣ ሊዮነል ሜሲ ጎል ሲያስቆጥር በከፍተኛ ሁኔታ መደሰቱ፣ መሃል ላይ መተኛቱ እንዲሁም አርጀንቲና ሁለተኛ ጎል ስታስቆጥር የመሃል ጣቱን ሁለት ጊዜ ማሳየቱ ለሚዲያዎች ትኩስ ወሬ ነበር።
ማራዶና ባለ ብዙ ስሙ፣ ለተጨቋኞች አዛኝ፣ አዝናኝ፣ ታላቅ፣ ቁጡ፣ የሚያዋርድና ሌሎች የተባለው ታላቁ እግር ኳሰ ተጨዋች ይህችን ዓለም ቢሰናበትም ህይወቱን የኖረበት መንገድ ለወደፊት ትውልድ የሚዘከረው፣ በእግር ኳስ ችሎታው የማይሞት ስምና አሻራ ትቶ አልፏል።

የፎቶው ባለመብት, AFP












