ከማራዶና አስከሬን ጋር ፎቶ የተነሱ የቀብር ሠራተኞች ጉዳይ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከሰሞኑ ህይወቱ ያለፈውን ድንቁን እግርኳስ ተጫዋች ዲያጎ ማራዶና የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ሊያስፈፅሙ የተቀጠሩ ሠራተኞች ከአስከሬኑ ጋር ፎቶ በመነሳታቸው ውግዘት እያስተናገዱ ነው።
ረቡዕ ኅዳር 16/ 2013 ዓ.ም ህይወቱ ያለፈው የማራዶናን የቀብር ሥነ ሥርዓት ለማስፈፀም ኃላፊነቱን በዋነኝነት የወሰደው ድርጅት ለሥራው የቀጠራቸው ሦስት ግለሰቦች ናቸው ፎቶ ሲነሱ የሚታዩት።
ለሕዝብ ይፋ በሆኑት ሁለት ፎቶዎች ላይ ግለሰቦቹ የሬሳ ሳጥኑ ክፍት ሆኖ እየሳቁና፣ እጃቸውንም ከፍ አድርገው የአውራ ጣታቸውን ምልክት ያሳዩበታልም ተብሏል።
ፎቶዎቹም ከፍተኛ ውግዘትና ቁጣን ቀስቅሷል።
የማራዶና ተወካይና ጠበቃ ማቲያስ ሞርላ በበኩላቸው አፀያፊ ነገር እንደተከናወነ ጠቅሰው፤ ፎቶውን ያወጡት አካላት በሕግ አግባብ እጠይቃለሁ ብለዋል።
"ለጓደኛዬ ትዝታ ስል ይህንን የጭካኔ ተግባር የፈፀመውን ሳልፋረዳው አልተኛም" በማለት ሞርላ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
በቦነስ አይረስ ሴፒሎስ ፒኒየር የቀብር አስፈፃሚ ሥራ አስኪያጅ ማቲያስ ፒኮን ለአገሪቱ ሚዲያ እንደተናገሩት በፎቶው ላይ የሚታዩት ሦስት ሰዎች የሬሳ ሳጥኑን ለማንቀሳቀስ ረዳት አድርገው የተቀጠሩ ናቸው ብለዋል።
"በተፈጠረው ነገር በጣም ነው ያዘንነው" በማለት ማቲያስ ፒኮን ለኒውስ ቻናል ተናግረዋል።
"ቤተሰቡ እኛን አምኖ ነበር፤ ከቤተሰቡም ጋር ለረዥም ጊዜ አብረን ሰርተናል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Casa Rosada
ማቲያስ ፒኮን እንዳሉት ኩባንያቸው ከዚህ ቀደምም ለማራዶና ቤተሰቦች የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዳዘጋጁም ገልፀዋል።
"ቤተሰቦቹ በእኛ ሥራ ይተማመናሉ፤ ለዚያም ነው ይህ ተግባር ልባችንን የሰበረው" በማለት ተናግረዋል።
አክለውም "የ75 ዓመቱ አባቴ እያለቀሰ ነው፣ እኔም እያለቀስኩ ነው ወንድሜም እንዲሁ። በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶናል" በማለት ተናግረዋል።
የማራዶና የቀድሞ ባለቤት ክላውዲያ ቪላፋኔን ስለፎቶዎቹ ሲነገራት በጣም ተበሳጭታ እንደነበረም ማቲያስ ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የማራዶና ቤተሰቦች ሕጋዊ እርምጃ ይውሰዱ ማቲያስ ባያውቁም፤ ሆኖም እስካሁን ድረስ ከፎቶዎቹ ጋር ተያይዞ ወንጀል ሪፖርት እንዳልተደረገ ቴላም የተባለ የዜና ወኪል የፍትህ አካላትን ምንጭ አድርጎ ዘግቧል።
ማራዶና በትናትንናው ዕለት የተቀበረ ሲሆን ህልፈተ ህይወቱንም ተከትሎ የሦስት ቀን ሐዘን በአገሪቱ ታውጇል።
የሬሳ ሳጥኑ በአርጀንቲና ሰንደቅ አላማ እንዲሁም እግር ኳስ ሲጫወት መለያው በነበረው አስር ቁጥር ማልያ ተሸፍኖ በቦነስ አይረስ የፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ሕዝቡ እንዲሰናበተው ተደርጓል።
በሺህዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቹም የእግር ኳስ ጀግናቸውን ለመሰናበት መጥተው ነበር፤ ሆኖም ፖሊስና በሰልፍ ላይ የነበሩ ለቀስተኞች መጋጨታቸውን ተከትሎ የስንብት ፕሮግራሙ በአጭር ተቋጭቷል።
በበርካቶች ዘንድ የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የሚወደሰው ማራዶና በልብ ህመም ቦነስ አይረስ አቅራቢያ በምትገኘው ትግሬ ከተማ በቤቱ ውስጥ ነው ህይወቱ ያለፈው።












