አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ጥበበኛ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና አረፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከምድራችን የእግር ኳስ ኮከብ ተጫዋቾች መካከል ከቀዳሚዎቹ ውስጥ የሚጠቀሰው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በ60 ዓመት ዕድሜው አረፈ።
የቀድሞው የአርጀንቲና ኮከብ ተጫዋች እና በኋላም የአገሩ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ያረፈው ቤቱ ውስጥ ሳለ በልብ ችግር እንደሆነ ተገልጿል።
ማራዶና በዚህ ወር መጀመሪያ አካባቢ በአንጎሉ ውስጥ ላጋጠመው የደም መርጋት የተሳካ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለት የነበረ ሲሆን በተከታይነትም ከአልኮል ሱስ ለመላቀቅ ሕክምና ይደረግለታል ተብሎ ነበር።
የዓለማችን የምንጊዜም ታላላቅ ተጫዋቾች ከሚባሉት አንዱ የሆነው ማራዶና አርጀንቲና እአአ በ1986 የዓለም ዋንጫ ባለቤት ስትሆን የቡድኑ አምበል የነበረ ሲሆን ድንቅ ችሎታውንና የታወቀባቸውን የኳስ ጥበቡን በማሳየት ዓለምን አስደምሞ ነበር።
በተለይ በወቅቱ አርጀንቲና ከእንግሊዝ ጋር ባደረገችው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ እሱ "የእግዜር እጅ" ያላትና ዳኞች ሳያዩ በእጁ ያስቆጠራት ግብ ዘወትር ትታወሳለች።
በተጨማሪም ለስፔኑ ባርሴሎናና ለጣሊያኑ ናፖሊ ቡድኖች በአውሮፓ ውስጥ የተጫወተ ሲሆን፤ በጣሊያን ሴሪ አ ውስጥም ሁለት ጊዜ ዋንጫ ለማንሳት በቅቶ ነበር።
የአርጀንቲና እግር ኳስ ማኅበር የማራዶና ሞት በተሰማ ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጣው መግለጫ "በጀግናችን ሞት በጣሙን አዝነናል" በማለት "ሁልጊዜም በልባችን ውስጥ ትኖራለህ" ብሏል።
ማራዶና ለአገሩ አርጀንቲና በአራት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ በተደረጉ 91 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 34 ግቦችን አስቆጥሯል።
ማራዶና የተከለከሉ አበረታች መድኃኒቶችንና ዕጽ በመጠቀም ስሙ በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ ሲሆን ከስፖርትም እገዳ ተጥሎበት ነበር።
ማራዶና ፕሮፌሽናል እግር ኳስን ከዛሬ 23 ዓመት በፊት በ37 ዓመት ዕድሜው ያቆመ ሲሆን፤ በአርጀንቲና ውስጥ ያሉ ቡድኖችን በአሰልጣኝነት ከመራ በኋላ የአገሩን ብሔራዊ ቡድንንም በማሰልጠን ለዓለም ዋንጫ አብቅቷል።
ከዚያም በኋላ በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና በሜክሲኮ ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችን በተለያዩ ጊዜያት አሰልጥኖ ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ደግሞ የአገሩን አንድ ቡድን በማሰልጠን ላይ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












