ታላቁ የኤቨረስት ተራራ በአንድ ሜትር አድጓል ተባለ

የኤቨረስት ተራራ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የኤቨረስት ተራራ

በአለማችን ትልቁ ተራራ፣ኤቨረስት አንድ ሜትር በሚጠጋ (0.86 ሜትር) የእርዝማኔ ብልጫ አሳይቷል ተባለ።

የተራራው እርዝመት ከዚህ ቀደም ከተመዘገበበት በአንድ ሜትር በሚጠጋ ብልጫ ማደጉንም የኔፓልና የቻይና ባለስልጣናት አሳውቀዋል።

አገራቱ በተራራው እርዝመትም ተስማምተው የማያውቁ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ሁለቱም 8 ሺህ 848̇.86 ሜትር እርዝማኔ አለው ብለዋል።

ቻይና ከዚህ ቀደም በልኬቴ መሰረት 8 ሺህ 8444.43 ሜትር ነው ስትል የነበረ ሲሆን ይህም ኔፓል ለካሁት ከምትለው በአራት ሜትር ያንስ ነበር።

ኤቨረስት ተራራ በቻይናና በኔፓል መካከል የሚገኝ ሲሆን በሁለቱም አገራት በኩል ተራራውንም መውጣት ይቻላል።

ከኔፓል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተውጣጡ ባለስልጣናት እንዲሁም ቦታዎችን በበላይነት የሚቃኘው ድርጅት እንዳሳወቁት ሁለቱም አገራት በመተባበር እንደተሳተፉበትና በአዲሱም ልኬት መስማማታቸውን ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የአለማችን ትልቁ ተራራ ማደግ ሁኔታንም በጥምረት ነው ያወጁት።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ ወደ ኔፓል መዲና ካታማንዱም ባቀኑበትም ወቅት ነው በአንድ ላይ የገለፁት።

ሆኖም የተራራው እርዝማኔ ለምን ልዩነት አመጣ የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም።

የቻይና ባለስልጣናት የኤቨረስት ተራራ መለካት ያለበት ድንጋዩ መጨረሻ ድረስ ነው ሲሉ ኔፓል በበኩሏ ተራራውን የሸፈነው በረዶም ሊካተት ይገባል በማለትም ትከራከር ነበር።

የቻይና የቅኝት ሰራተኞች አገሪቷ በጎሮጎሳውያኑ 2005 ተራራውን በለካችበት ፀንተው ቆይተው ነበር። የኔፓል የመንግሥት ባለስልጣናት በበኩላቸው ቻይና የራሷን ልኬት እንዲቀበሉ ከፍተኛ ጫና እያሳደረችባቸው እንደሆነ ለቢቢሲ በጎሮጎሳውያኑ 2012 ተናግረው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ኔፓል የራሷን የተራራ ልኬት ማድረግ እንዳለባትም ውሳኔ ላይ ደርሳለች።

ኔፓል የኤቨረስት ተራራ 8 ሺህ 848 ሜትር እርዝማኔ አለው ስትል የነበረው ህንድ በ1954 ካደረገችው ቅኝትና ልኬት ተነስታ ነው።

በመጨረሻም አገሪቷ የተራራውን ልኬት ለመጀመሪያ ጊዜ አከናውናለች። አራት የኔፓል የመሬት ቅኝት ሰራተኞችም ለሁለት አመት ያህል ስልጠና ወስደዋል።