ኮሮናቫይረስ ፡ የ90 ዓመቷ አዛውንት የፋይዘር/ባዮንቴከ ክትባትን በመከተብ በዓለም የመጀመሪያዋ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ዩናይትድ ኪንግደም ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ዛሬ ለዜጎቿ መስጠት ስትጀምር የዘጠና ዓመቷ አዛውንት የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባትን በመውሰድ በዓለም የመጀመሪያዋ ሆኑ።
በሰሜን አየርላንድ ኢኒስኪለን ነዋሪ ሆኑት የዘጠና ዓመቷ የእድሜ ባለጸጋ ማርግሬት ኪናን የፋይዘር/ባዮንቴክ የኮቪድ-19 ክትባትን ከሙከራ ውጪ በመውሰድ በምድራችን የመጀመሪያዋ ሰው ሆነዋል።
አዛውንቷ ማርግሬት በመርፌ የሚሰጠውን ክትባት ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ በኮቬንትሪ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሚገኘው የክትባት ማእከል ተገኝተው ነው የወሰዱት።
አሁን መሰጠት የተጀመረው የኮቪድ-19 ክትባት በዋናነት ትኩረት ያደረገው ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች ሲሆን በቀጣይም ለሌሎች እንደሚዳረስ ተነግሯል።
በመላው ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚገኙ ከ70 በላይ የሚሆኑ ሆስፒታሎች እድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ ለሆኑ አዛውንቶች እና ለጤና ባለሙያዎች ክትባቱን ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተገልጿል።
የአሜሪካ እና የጀርመን ኩባንያ የሆኑት ፋይዘር እና ባዮንቴክ ያበለጸጉት ክትባት ዩናይትድ ኪንግደም ለዜጎቿ እንዲሰጥ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን መፍቀዱ ይታወሳል። በዚህም ዩኬ ይህን ክትባት በመጠቀም የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
ክትባቱን ዛሬ ከሚወስዱት መካከል የ87 ዓመቱ ዶ/ር ሃሪ ሹክላ አንዱ ናቸው። ዶ/ር ሃሪ ክትባቱን ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ኒውካስትል በሚገኝ ሆስፒታል እንደሚወስዱ ገልጸው በዚህም ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የክትባት አሰጣጥ መረሃ ግብሩ ቅድሚያ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑትን በማስቀደም ሕይወት ወደቀደመ መልኩ እንድትመለስ ይረዳል ተብሏል።
"ቪ-ዴይ" ወይም የድል ቀን የሚል ስያሜ በተሰጠው ዕለት የሚጀመረው የክትባቱ መርሃ ግብር፤ ዜጎች ክትባቱን የመከተብ ግዴታ አይኖርባቸውም ተብሏል።
ጠቅላይ ሚንሰትር ቦሪስ ጆንሰን፤ "ዩናይትድ ኪንግደም ከኮሮናቫይረስ ጋር በምታደርገው ትግል የዛሬዋ ቀን ሌላ ምዕራፍ ከፍታለች" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ክትባቱን ለዜጎች ለማዳረስ ወራትን ሊፈጅ እንደሚችል አስታውሰው እስከዚያው ድረስ ግን መንግሥት ያስተላለፋቸው የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን ዜጎች እንዲተገብሩ አስታውሰዋል።
እስካሁን በዩናይትድ ኪንግደም ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ከ60ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
መንግሥት በአሁኑ ወቅት 800 ሺህ የክትባት ብልቃጦችን ዝግጁ ያደረገ ሲሆን ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ክትባቶችንም አዟል። ይህም ለ20 ሚሊዮን ሕዝብ በቂ ነው።
95 በመቶ ቫይረሱን የመከላከል አቅምን ያጎለብታል የተባለለትን ክትባት ሰዎች በ21 ቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ መወጋት ይኖርባቸዋል። ሰዎች ከቫይረሱ እራሳቸውን መከላከያ የሚጀምሩት ሁለተኛውን ክትባት ከወሰዱ ከሰባተኛው ቀን በኋላ ነው ተብሏል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ክትባቱን የያዙ ማቀዝቀዣዎች ከሚመረቱበት ቤልጄየም ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሲገቡ ቆይተዋል። በቀጣይ ሦስት ሳምንታት ውስጥም ተጨማሪ 10 ሚሊዮን የክትባት ብልቃቶች ወደ ዩኬ ገብተው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይሰራጫሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከሳምንታት በኋላ ደግሞ በስታዲየሞች እና በግዙፍ መሰብሰቢያ አዳራሾች ለበርካታ ሰዎች በአንድ ጊዜ ክትባት መስጠት ይጀመራል ተብሏል።
















