'ጩኸቱ በጠበጠኝ" በሚል አውራ ዶሮ ተኩሶ የገደለው በእስር ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፈረንሳይ ውስጥ አንድ ግለሰብ 'ጩኸቱ በጠበጠኝ' በሚል ሰበብ የጎረቤቱን ዶሮ ተኩሶ በመግደሉ በአምስት ወራት እስራት ተቀጥቷል።
ሰውዬው አውራ ዶሮውን ተኩሶ መግደሉ አልበቃ ብሎት በፌሮ በሳስቶታል ተብሏል።
ማርሴል የሚል መጠሪያ የነበረው አውራ ዶሮ የተገደለው ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ነበር።
ገዳዩ ግለሰብ አውራው ዶሮ ከአቅሙ በላይ እየጮኸ ሰላሜን ነስቶኛል በሚል ምክንያት ነው ድርጊቱን የፈፀመው ተብሏል።
የማርሴል ባለቤት የሆነው ሴባስቲያን ቨርኒ 'ፍትህ ለአውራ ዶሮዬ' በሚል በበይነ መረብ ፊርማ ማሰባሰብ ጀምሯል።
እሳካሁን ድረስ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች 'ፍትህ ለማርሴል' ሲሉ ፊርማቸውን አሳርፈዋል።
ገዳዩ የጎረቤት እንስሳ ላይ ግፍ በመፈፀምና በሌሎች ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
ከተፈረደበት የአምስት ወራት እስር በተጨማሪ 300 ዩሮ እንዲቀጣ ዳኛው ፈርደውበታል።
አውራ ዶሮ በጭካኔ ገድሏል የተባለው ግለሰብ ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ማንኛውንም ዓይነት የጦር መሣሪያ እንዳይዝም ታግዷል።
ለአውራ ዶሮው ፍትህ ፊርማ እያሰባሰበ ያለው ሴባስቲያን ግን "ምንም ቢሆን አውራ ዶሮዬ ላይ የተፈፀመውን ግፍ አይመልስልኝም" ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል ድምፁን አሰምቷል።
አውራ ዶሮው በመገደሉ ምክንያት እሱና ቤተሰብ ከፍተኛ ሃዘን ላይ እንዳሉም ተናግሯል ሴባስቲያን።
በገጠራማዋ አርዴቼ ከተማ ነዋሪ የሆነው የአውራ ዶሮው ባለቤት የመንደሩ ሰዎች እንሳስቶቻቸው ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም እንዲከላከሉ ጥሪውን አቅርቧል።
"ቀጣይ ማነው? የሚድሁ ኤሊዎች፤ የስንዴ ሽውታ፤ ቲማቲም፤ ወይስ የአህያ ጩኸት?" በማለት ምሬቱን አሰምቷል።
ፈረንሳይ ውስጥ አውራ ዶሮን በተመለከተ አስገራሚ ዜና መስማት የተለመደ ነው።
ባለፈው ዓመት አንድ የሃገሪቱ ፍርድ ቤት የጎረቤታችን አውራ ዶሮ ጩኸት በጠበጠን ሲሉ የከሰሱ ሰዎችን ቅሬታ ውድቅ በማድረግ 'የአውራ ዶሮው የመⶐህ' መብት እንዲከበር መበየኑ ይታወሳል።
መብቱ የተከበረለት ማውሪስ የተሰኘው አውራ ዶሮ ግን ብዙም ሳይቆይ በስድስት ዓመት ይህቺን ዓለም ተሰናብቷል።












