ትግራይ፡ የጠ/ሚ ጽሕፈት ቤት ህወሓት የትጥቅ ትግል የማድረግ አቅም የለውም አለ

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አርማ

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE

የህወሓት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ መሸነፉንና ተበታትኖ ባለበት ሁኔታ የተራዘመ የሽምቅ ውጊያ ማድረግ በሚችልበት አቋም ላይ እንዳልሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ በትግራይ ክልል እተካሄደ ያለው ሕግን የማስከበር ዘመቻ አሁን ያለበትን ደረጃ በተመለተ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው መቀለ ከሳምንት በፊት "ሰላማዊ ሰዎች ሳይጎዱና ንብርት ሳይወድም" በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ከገባች በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው ተጠናቋል ብሏል።

ነገር ግን ከዋና ከተማዋ መቀለ የወጡት የትግራይ ኃይሎች አመራሮች ለተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች እንደተናገሩት ውጊያው እንዳላበቃና ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተው ነበር።

ይህንንም በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሚንስትር የሆኑት ዛዲግ አብረሃ በበኩላቸው፤ በክልሉ ጦርነት እየተካሄደ አለመሆኑንና ህወሓት ጦርነት የማካሄድ ቁመና እንደሌላው ጠቅሰው በወንጀል የሚፈለጉ የቡድኑ አመራሮችን ለመያዝ የሚደረግ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው አርብ ተባበሩት መንግሥታት ባለስልጣናት ለፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደተናገሩት በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በቀጠለው ውጊያ ምክንያት እርዳታ ለማቅረብ የሚያደርጉትን ጥረት እንደተስተጓጎለባቸው ተናግረው ነበረ።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ሰኞ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ ላእ እንዳመለከተው የፌደራል መንግሥት በአሁኑ ተልዕኮ በሕግ የሚፈለጉ የህወሓት አመራሮችን ይዞ ለሕግ ማቅረብ፣ ሕግና ሥርዓትን ማረጋገጥ እንደሆነ አመልክቷል።

በተጨማሪም በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ፣ ግጭቱን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱትን ወደ ቀያቸው መመለስ፣ የትራንስፖርት እና የግነኙነት መስመሮችን ጠግኖ ሥራ ማስጀመር እንደሆነ ገልጸወል።

"ህወሓት በሐሰት ኃይሎቹ በጦርነት የተፈተኑና የታጠቁ መሆናቸውን በመጥቀስ በትግራይ ተራራማ ቦታዎች ላይ የተራዘመ የትጥቅ ትግል ማካሄድ ይችላሉ ሲል ነበር" ያለው መግለጫው "እውነታው ግን ህወሓት ሙሉ በሙሉ ተሸንፏል፤ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ የትጥቅ ትግል የመከፍት አቅምም እየለውም" ብሏል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ጨምሮም ህወሓት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ዓለም አቀፍ መልክ እንዲኖረው መሞከሩን አመልክቶ፤ "ሐሰተኛ ክሶችን እንደ መጨረሻ አማራጭ በመደርደር ዓለም አቀፍ ድርድር እንዲኖር ጫና በማሳደር ከተጠያቂነትና ከፍትሕ ለማምለጥ ጥረት አድርጓል" ይላል የጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጫ።

በአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እና በማይካድር ከተማ ንሑሃን ዜጎች ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት እንዲሁም በባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ላይ የተፈጸሙ የሮኬት ጥቃቶችን በመስታወስ፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት "ቡድኑ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት ያሳስበኛል ለማለት የሚያስችል ሞራል ሊኖረው አይችልም" ብሏል።

የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ የፌደራል መንግሥቱ ቀዳሚ ትኩረት እንደሚሆን በመጥቀስም ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ጋር በመሆን በግጭቱ ምክንያት ለችግር የተጋለጡትን በትግራይ ውስጥ ባሉ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሚገኙትን የሌላ አገር ዜጎችን ጭምር ለመርዳት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

line

በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው ውዝግብ ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ተካሮ ቆእቶ ነበር።

አለመግባባቱና መካሰሱ ያለማቋረጥ በቀጠለበት ሁኔታ ጥቅም 24/2013 ዓ.ም ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ክልል በነበሩት የሠሜን ዕዝ አባላት ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ካደረጉ በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት በህወሓት ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል።

ለሦሰት ሳምንታት ያህል በዘለቀው ወታደራዊ ዘመቻ የትግራይ መዲና መቀለ ጨምሮ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች በፌደራል መንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ሰር ከዋሉ በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከአንድ ሳምንት በፊት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።