ባይደን የቀድሞውን ጄኔራል ለመከላከያ ሚኒስትርነት አጩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተመራጩ የዩናይት ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጡረት የወጡትን ጀኔራል ሎይድ ኦስቲንን ለመከላከይ ሚኒስትርነት ማጨታቸው ተሰምቷል።
ጄኔራል ሎይድ ኦስቲን ሹመታቸው ከፀደቀ ፔንታጎን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመሩ ጥቁር አፍሪካዊ አሜሪካዊ ይሆናሉ።
በፕሬዝደንት ባራካ ኦባማ ዘመነ መንግሥት የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ አዛዥ ሆነው ያገለገሉት ጄኔራል ኦስቲን ጡረታ ከወጡ ሰባት ዓመት ስላልሞላቸው ከኮንግረሱ ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
ባይደን ከሁለት ሳምንት በፊት የብሔራዊ ደህንነት ሹም ይሆናሉ የተባሉት ዕጩዎችን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ባይደን ጄኔራሉን ማጨታቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ይዘግቡት እንጂ ባይደንም ይሁኑ ጄኔራል ኦስቲን እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ጆ ባይደን ነባሯ የፔንታጎን ባለሥልጣን ሚሼል ፈሎርኖይ የመከላከያ ሚኒስትር ይሆናሉ የሚል ግምት አለ ብለው ዘግበው ነበር።
ሚሼል ዕጩ ሆነው ቀርበው ሹመታቸው ቢፅድቅ ኖሮ የመጀመሪያ ሴት የመከላከያ ሚኒስቴር ይሆኑ ነበር።
በፈረንጆቹ ኅዳር 3 አሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ አካሂዳ ጆ ባይደን አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።
የዴሞክራት ፓርቲው ዕጩ በሚቀጥለው ጥር በኦፊሴላዊ በዓለ ሲመት መንበረ ሥልጣኑን ከፕሬዝደንት ትራምፕ ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ነገር ግን ፕሬዝደንት ትራምፕ እስካሁን ድረስ የምርጫውን ውጤት አምነው አልተቀበሉም። እስካሁን ድረስ ማስረጃ ማቅረብ ባይችሉም ምርጫው ተጭበርብሯል ሲሉ ያማርራሉ።
ጄኔራል ኦስቲን ማናቸው?
ፖለቲኮ የተሰኘው ጋዜጣ ነው ጄኔራል ኦስቲን የመከላከያ ሚኒስትር ለመሆን ታጭተዋል ሲል የዘገበው።
ጄኔራል ኦስቲን ይህንን ቦታ ያገኛሉ ብሎ ብዙ ሰው እንዳልጠበቀ ጋዜጣው ይናገራል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሰውየው ስም በጉልህ መሰማት ተጀምሯል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ደግሞ ከበርካታ ሰዎች አጣርቻለሁ ሲል ዘግቧል።
ሰውዬው ለዚህ ቦታ ሊታጩ የቻሉት ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ጥቁር አሜሪካዊያን፣ እስያዊያንና ላቲን አሜሪካዊያን እንዲያጩ ከመብት ተሟጋቾች ተደጋጋሚ ጥሪ ስለቀረበላቸው ይሆናል ብሏል።
ሲኤንኤን በበኩሉ ደግሞ ውስጥ አዋቂ ነገረኝ ብሎ ባወጣው ዘገባ ባይደና ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ነው ጄኔራል ኦስቲን የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሆኑ የጠየቋቸው እሳቸውም እሺታቸውን ሰጥተዋል ብሏል።
ባለ አራት ኮከቡ ጄኔራል ከ2013 እስከ 2016 ባለው ጊዜ የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
በወቅቱ መካከለኛው ምስራቅ፣ እንዲሁም ማዕከላዊና ደቡባዊ እስያን ይመለከቱ ነበር ተብሏል።
ከዚህ ኃላፊነታቸው በፊት የአሜሪካ ወታደር ምክትል ጠቅላይ አዛዥና በኢራቅ የአሜሪካ ወታደሮች አዛዥ ሆነው አገልግለዋል።
በእነዚህ ዓመታት ከያኔው ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር በቅርበት ይሰሩ እንደነበርም ይነገርላቸዋል።












