ኮሮናቫይረስ ፡ ዩናይትድ ኪንግደም የኮቪድ-19 ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቀደች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩናይትድ ኪንግደም ፋይዘርና በባዮንቴክ የተሰራው የኮሮናቫይረስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል በመፍቀድ ከዓለማችን ቀዳሚዋ አገር ሆናለች።
የብሪታኒያ መድኃኒት ቁጥጥር መሥሪያ ቤት 95 በመቶ የኮሮናቫይረስን ይከላከላል የተባለለት ይህንን ክትባት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል ብሏል።
ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ የሚባሉ ሰዎች ክትባቱን በወሰዱ በቀናት ውስጥ ሰውነታቸው መከላከያ ያዳብራል ተብሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም ፋይዘርና ባይንቴክ የተባሉት አምራቾች ከሚያመርቱት ክትባት ውስጥ 40 ሚሊዮን ይድረሰኝ ስትል አዛለች።
በሽታውን ለመከላከል አንድ ሰው ክትባቱን ሁለት ጊዜ መወጋት አለበት።
ይህ ማለት 40 ሚሊዮን ክትባት ለ20 ሚሊዮን ሰው ይበቃል ማለት ነው።
አምራቹ 10 ሚሊዮን ክትባት ለዩናይትድ ኪንግደም በቅርብ ቀናት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ፋይዘር በ10 ወራት ጊዜ ውስጥ ክትባት ማምረት የቻለ የመጀመሪያ አምራች ነው።
ክትባት አዘጋጅቶ በማምረት ጥቅም ላይ ለማዋል ብዙ ጊዜ ዓመታትን የሚፈጅ ሂደት የነበረ ሲሆን ለኮሮናቫይረስ ግን በአጭር ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል።
የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ሚኒስትሩ ማት ሃንኮክ በትዊተር ገፃቸው "እርዳታ እየመጣ ነው። ሰዎች በሚቀጥለው ሳምንት ክትባቱን ማግኘት ይጀምራሉ" የሚል መልዕክት አስተላፈዋል።
ባለሙያዎች ክትባቱ ጥቅም ላይ መዋል ቢጀምር እንኳ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ሕግጋትን አሁንም ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀምና ተመርምረው ኮሮናቫይረስ ያለባቸውን ሰዎች በማግለያ ጣብያዎች ማቆየት አሁንም ይቀጥላሉ ተብሏል።
ክትባቱ ምን አይነት ነው?
ኤምአርኤንኤ የተሰኘ ስያሜ ያለው አዲስ ክትባት ሲሆን ከኮሮናቫይረስ ቅንጣት ተወስዶ የተሰራ ነው።
ክትባቱ የሰው ልጅ ሰውነት ቫይረሱን እንዲላመደውና የመከላከል ኃይሉን እንዲያደራጅ ያደርገዋል።
ክትባቱ ከዜር በታች 70 ዲግሪ ሴልሲዬር በሆነ ቅዝቃዜ ውስጥ መቀመጥ ይኖርበታል።
ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር ለክትባቱ ተብሎ በተዘጋጀ ሳጥን ውስጥ በደረቅ በረዶ ታሽጎ መሆን አለበት።
ባለሙያዎች ይህን ክትባት ቀድመው ማግኘት ያለባቸው ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ናቸው ይላሉ።
በአረጋውያን ማቆያ ውስጥ ያሉ፤ በተለይ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ80 በላይ የሆኑ ሰዎችና የጤናና ማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በቅዳሚያ ከላይ ለተጠቀሱት የሕብረተሰቡ አባላት ከተዳረሰ በኋላ ከ50 ዓመት በላይ ላሉ ሰዎችን ጨምሮ ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው ወጣቶች ክትባቱ እንደሚሰጥ ተነግሯል።
ክትባቱ ሁለት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን የመጀመሪያው ከተሰጠ ከ21 ቀናት በኋላ ሁለተኛው ይሰጣል።
ከፋይዘር በተጨማሪ ሌሎች ተስፋ የተጣለባቸው ክትባቶች ፈቃድ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ሞደርና የተባለ አንድ ክትባት ከዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ፈቃድ ለማግኘት ጠይቋል።
ዩናይትድ ኪንግደም ከዚህ አምራች 7 ሚሊዮን ክትባት ለመግዛት ቅድመ ትዕዛዝ አስገብታለች።
ሌላኛው ክትባት ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲና አስትራዜኔካ የሚያመርቱት ነው።
ሩሲያ የራሷን ስፑትኒክ 5 የተሰኘ ክትባት አምርታ ጥቅም ላይ እያዋለች እንደሆነ ካሳወቀች ሰንበትበት ብላለች።
የቻይና ጦር ሠራዊትም ክትባት አምርቶ እየተጠቀመ እንደሆነም አሳውቋል።
















