ኮሮናቫይረስ ፡ ኬንያ ባለስልጣኖቿ የኮቪድ-19 ክትባትን ከቻይና እንዲፈለጉ አዘዘች

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የአገራቸው የጤና ባለስልጣናት ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚሆን ክትባት ከቻይና እንዲያፈላልጉ አዘዙ።

ኬንያ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው በቅርቡ አገልግሎት ላይ ይውላሉ ከተባሉት ክትባቶች ምዕራባዊያን ባለጸጋ አገራት 3.8 ቢሊዮን የክትባት ምርት ለመግዛት ማዘዛቸው ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው።

በዚህም መሠረት ፕሬዝዳንት ኬንያታ የጤና ጥበቃ መስሪያ ቤታቸው ቻይና እያዘጋጀች ካለው ክትባት ውስጥ ለዜጎቻቸው የሚሆን እንዲገዛ አዘዋል።

"ኬንያ ውስጥ ኮሮናቫይረስ በከፋ ሁኔታ ተመልሶ እየተከሰተ ይመስላል፤ በተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ያለው የበሽታው መስፋፋት እየጨመረ ነው" ያሉት የኬንያ ጤና ሚኒስትር ሙታሂ ካግዌ ናቸው።

በተለያዩ አገራት ውስጥ እየተዘጋጀ ያለው የኮቪድ-19 ክትባትን በተለይ ለታዳጊ አገራት ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተደራሽነቱ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ዢንፒንግ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ቃል እንደገቡት፤ ቻይና እያደረገችው ያለው የክትባት ሙከራ ውጤታማ ሆኖ ከተሳካ ለአፍሪካ አገራት በርካሽ ዋጋ እንደሚያቀርቡ ተናግረው ነበር።

በሽታው መጀመሪያ በአገሯ የተከሰተው ቻይና በወረርሽኙ አያያዟ በኩል ብዙ ትችት ቀርቦባት ነበር። ክትባቱን ለአፍሪካ አገራት በቅናሽ አቅርባለሁ ማለቷም የተሰነዘረባትን ወቀሳ ለማርገብ ጥሩ እርምጃ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአሁኑ ጊዜ ኬንያ ውስጥ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና በመድኃኒት አምራቹ አስትራዜኒካ አማካይነት የተዘጋጀው ክትባት ሙከራ እየተደረገበት ነው።

ቻይና እያዘጋጀችው ያለው ክትባት ሙከራ እየተደረገባቸው ካሉ አራት አገራት መካከል ከአፍሪካ ግብጽና ሞሮኮ ይገኙበታል።

የቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንዳለው፤ በአገሪቱ ውስጥ የተዘጋጁና አስፈላጊው ምርምር ተደርጎባቸው በሦስተኛ ደረጃ ክሊኒካዊ ሙከራ ላይ የሚገኙ አምስት የክትባት አይነቶች አሉ።

ምንም እንኳን ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ የሚያመለክት መረጃ ባይወጣም ኬንያ በአገሯ ውስጥም ክትባት ለመስራት ምርምር እያደረገች ትገኛለች።

በአሁኑ ጊዜ በኬንያ ውስጥ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ በበሽታው ሰበብም ከ1,400 በላይ ሰዎች በአገሪቱ ውስጥ ለሞት ተዳርገዋል።