ኮሮናቫይረስ ፡ ለ7.7 ቢሊዮን የዓለም ሕዝብን እንዴት ክትባት ማዳረስ ይቻላል?

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቻይና የተቀሰቀሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ተሰራጭቶ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ገድሏል። ከ63 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

የወረርሽኙን መስፋፋት ሊገቱ ይችላሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው በርካታ የኮቪድ-19 ክትባቶች ውጤታማ ሆነዋል።

በርካታ መድኃኒት አምራቾች ያበለጸጓቸውን የኮቪድ-19 ክትባቶች ለተጠቃሚዎች ለመስጠት ከመድኃኒት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ይሁንታን እየጠባበቁ ይገኛሉ።

ባለሙያዎች ክትባቶቹ ለሰው ልጆች እንዲሰጡ ፍቃድ ቢሰጥም፤ በመላው ዓለም በቢሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን ለመከተብ 5 ተግዳሮቶች ይጠብቁናል ይላሉ።

ተግዳሮት አንድ፡ ሰዎችን ማሳመን

አንድ ሰው ክትባቱን ከመከተቡ በፊት የክትባቱ ደኅንነት የተረጋገጠ ስለመሆኑ እና መከተብ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ማሳመን የመጀመሪያው ፈተና ይሆናል ይላሉ ባለሙያዎች።

ተግዳሮት ሁለት፡ ክትባቱን በሚፈለገው የቅዝቃዜ መጠን ውስጥ ማቆየት

ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ ክትባቶች መከማቸት ያለባቸው ከዜሮ በታች እስከ 80 ሴንቲ ግሬድ በሚደርስ ቅዝቃዜ ውስጥ ነው። ክትባቶቹ በሚፈለገው የቅዝቃዜ መጠን ውስጥ ካልተቀመጡ ይበላሻሉ ማለት ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ከሚገኙት የጤና ተቋማት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት ያላቸው 28 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ይላል።

ይህም ማቀዝቀዣ ፍሪጅ እና የመብራት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ወደሌለባቸው ስፍራዎች ክትባቱን ማጓጓዝ እና ማከማቸት ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ይጠቁማል።

ተግዳሮት ሦስት፡ የተማረ የሰው ኃይል

7.7 ቢሊዮን ሕዝብ ለመከተብ ቁጥሩ ከፍ ያለ የተማረ የሰው ኃይል ማስፈለጉ እሙን ነው።

አንዳንዱ ክትባት የትኛው የጤና ባለሙያ በቀላሉ መስጠት የሚችለው ቢሆንም አንዳንዶቹ ክትባቶች ግን የተለየ ሥልጠና መውሰድ ግድ ሊሉ ይችላሉ።

ተግዳሮት አራት፡ ሰዎችን ወደ ጤና ተቋም እንዲመጡ ማድረግ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ወደ አንድ የጤና ማዕከል ለመድረስ በርካታ ሰዓታትን በእግር መጓዝ ግድ ሊል ይችላል።

ይህም ብቻ አይደለም። በድህንት የሚኖር ቤተሰብ ክትባቱን ፍለጋ ለሰዓታት ተጉዞ የዕለት ምግቡን ሊያጣ ነው ማለት ነው።

በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሰዎች ክትባቱን ለመውሰድ ወደ ጤና ተቋም የመምጣት ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል።

ተግዳሮት አምስት፡ ድሃ አገራት ክትባቱን የማግኘታቸው ጉዳይ

እንደ ዩናይትድ ኪንገደም፣ አውስትራሊያ እና የአውሮፓ ሕብረት ገና ከአሁኑ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የክትባት ብልቃጦችን ለመግዛት ከአምራቾች ጋር ከስምምነት ደርሰዋል።

ይህ የሀብታም አገራት እሽቅድድም የድሃ አገራት ዜጎች ክትባቱን በፍጥነት እንዳያገኙ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ምንም እንኳን ጥቂት የማይባሉ ሀብታም አገራት 20 በመቶ ለሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ ክትባቱን ለማድረስ ቢስማሙም የደሃ አገራት ዜጎች ክትባቱን ለማግኘት አንድ ዓመት መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።