ኮሮናቫይረስ፡ አውስትራሊያ የኮሮና ክትባት በነጻ እሰጣለሁ አለች

የክትባት ምርምር

የፎቶው ባለመብት, UNIVERSITY OF OXFORD

አውስትራሊያ ኮቪድ-19 ክትባትን ለአገሬ ሕዝብ ሽራፊ ሳንቲም ሳልቀበል አድላለሁ ብላለች፡፡

አውትራሊያ 25 ሚሊዮን ለሚሆነው ሕዝቧ የምታድለውን ክትባት የምታገኘው ከእንግሊዝ ነው፡፡

አሁን በሙከራ ላይ ካሉ የክትባት ዜናዎች ሁሉ ላቅ ያለ ተስፋ የተጣለበት የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲው ክትባት ነው፡፡

ኦክስፎርድ ክትባቱን ከታዋቂው የመድኃኒት አምራች አስትራዜኔካ ጋር በመቀናጀት እያዳበረው ይገኛል፡፡

ይህ ክትባት በቀጣይ የሚደረጉ የመጨረሻ ምዕራፍ የክሊኒካል ሙከራዎች ስኬታማ ሆነው ከተጠናቀቁ አውስራሊያ ክትባቱን ለመግዛት ቀዳሚ አገር ሆና ተሰልፋለች ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን፡፡

ሞሪሰን እንደሚሉት ክትባቱን እያንዳንዱ ዜጋ እንዲወስድ ግዴታ ይጣልበታል፡፡

በአውስትራሊያ የሟቾች ቁጥር 450 አልፏል፡፡ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰውም በቪክቶሪያ ግዛት ነው፡፡

በዚህ ወር መጀመርያ አካባቢ ቪክቶሪያ የአስቸኳይ ጊዜ በመደንገግ ሰዎች ቤታቸው እንዲቀመጡ አስገድዳ ነበር፡፡ ይህም በሽታው ሥርጭት ከፍ ብሎ በመታየቱ ነው፡፡

አሁን በአውስራሊያ 7ሺ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ እንደተነኩ ይገመታል፡፡ ሆኖም አሁን በየቀኑ አዳዲስ ታማሚዎቸ ቁጥር እየጨመረ ሳይሆን እየቀነሰ ነው ያለው፡፡

የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና የአስትራዜኔካ ጥምረት እየተሞከረ ያለው ክትባት በዓለም ላይ አሁን ተስፋ ከተጣለባቸው አምስት ሙከራዎች በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው፡፡

አገራት ይህን ክትባት ወደ ገበያ ሲወጣ ቅድሚያ አግኝተው ለሕዝባቸው ለማድረስ ከፍተኛ ፉክክር ላይ ናቸው፡፡

የመጨረሻው የሙከራ ምዕራፍ ስኬታማ ሲሆን አውስራሊያ መድኃኒቱን በአገሯ ለማምረት ተዘጋጅታ ከወዲሁ ስምምነት ፈጽማለች፡፡ ሞሪስ እንደሚሉት ‹‹ወዲያው አምርተን ወዲያው 25 ሚሊዮን ሕዝባችንን እንከትባለን፡፡››

አንድ አገር ሙሉ ሕዝቧን ለመክተብ ምን ያህል ወጪ ያስወጣታል የሚለው ገና አልተሰላም፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አውስትራሊያ ሌላ ስምምነት አድርጋለች፡፡ ይህ ስምምነት 25 ሚሊዮን ዶላር አስከፍሏታል፡፡ ስምምነቱ ከአሜሪካ የመድኃኒት ቁሳቁስ አምራች ቤክተን ዲኪንሰን ጋር ሲሆን 100 ሚሊዮን መርፌና ስሪንጆችን ለማቅረብ የተደረገ ስምምነት ነው፡፡

አውስትራሊያ ከአስትራዜኔካ ጋር ያደረገቸው የክትባት ስምምነት በታሪኳ የመጀመርያው ነው፡፡

የአውስትራሊያ ሕዝብ መቼ ይከተባል ለሚለው ሚስተር ሞሪሰን ‹‹ክትባቱ የመጨረሻው ሙከራ ከተሳካ በመጪው ዓመት የመጀመርያዎቹ ወራት አውስትራሊያዊያን ይከተቡታል›› ብለዋል፡፡

ክትባት መከተብ ግዴታ ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁሉም ዜጋ የመከተብ ግዴታ ይጣልበታል ቢሉም ይህ አከራካሪ ጉዳይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ሞሪሰን መንግስታቸው በዚህ ረገድ ገና ፖሊሲ እየቀረጸ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለአንድ የአገሬው ራዲዮ ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሚስተር ሞሪሰን ‹‹በተለየ የጤና ምክንያት መድኃኒቱን ለመከተብ የማይገደዱ›› እንደሚኖሩ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

‹‹እያወራን ያለነው የዓለምን ምጣኔ ሀብት ስላንኮታኮተ ወረርሽኝ ነው፡፡ ሺዎችን ሕይወት ስለቀጠፈ ወረርሽኝ ነው፤ ክትባቱ አማራጭ ተደርጎ የሚወሰድ ይሆናል ብዬ አልጠብቅም›› ብለዋል አስገዳጅነቱ አይቀሬ መሆኑን ሲያስገነዝቡ፡፡

ሚስተር ሞሪሰን በትንሹ 95 ከመቶ አውስትራሊያዊያንን ለመከተብ እንደታሰበ አልሸሸጉም፡፡

ኮሮና
Banner