ሐሰተኛ ዜና፡ አነጋጋሪው የሩሲያ የኮሮናቫይረስ ክትባትና የፑቲን ጉዳይ

የምትከተበወ ሴት

የፎቶው ባለመብት, SECHENOV MEDICAL UNIVERSITY PRESS OFFICE

የምስሉ መግለጫ, በዓለም ዙሪያ ክትባቶች ላይ ሙከራ እየተደረገ ነው

ሩሲያ ላለፉት ወራት ሙከራ ስታደርግበት የነበረው ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ መስጠቷን ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ካሳወቁ በኋላ፤ በርካቶች ክትባቱ ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

ስለ ክትባቱ ሐሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቀልድ አዘል አስተያየቶች እየሰነዘሩ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙዎች ከተጋሯቸው ሐሳቦች ጥቂቱን እንመልከት።

ጀግናው ፑቲን

ፑቲንን በተመለከተ በተለያዩ ቋንቋዎች የለበጣ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።

በሆሊውድ ፊልሞች የሚታወቁ እንደ ስፓይደርማን እና አይረንማን ያሉ ልቦወለዳዊ ጀግኖችን ከፑቲን ጋር ያነጻጸሩ አሉ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ከተሰራጩ ፎቶዎች አንዱ ፑቲን ትልቅ የክትባት መርፌ ጀርባቸው ላይ አድርገው ድብ ሲጋልቡ ያሳያል።

ይህንን ፎቶ ፑቲን ራሳቸው አጋርተውታል የሚል ሐሰተኛ ወሬም ሲናፈስ ነበር።

ፑቲንን የሚደግፍ የፌስቡክ ገጽ ላይ ክትባቱን የሚደግፍ ጽሁፍ 200 ሺህ ጊዜ ተሰራጭቷል።

ይፋዊ የፑቲን ገጽ ባይሆንም በርካቶች የፕሬዘዳንቱ እንደሆነ ያምናሉ። በእርግጥ ፑቲን እምብዛም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አይገኙም።

በገጹ ላይ በርካታ ተመልካች ያገኘው ፎቶ የመጀመሪያውን የሶቪየት ኅብረት ሳተላይት ከኮቪድ-19 ክትባት ጋር ያነጻጽራል።

ሳተላይቱ “በሕዋ ለሰው ልጆች መንገድ የጠረገ ነው”፣ ክትባቱ ደግሞ “የሰው ልጆችን ከአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም ከአካላዊ ርቀት የሚታደግ ነው” ተብሏል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የክትባቱ አስተማማኝነት ላይ ጥያቄ ከማንሳቱ ባሻገር፤ የዓለም ጤና ድርጅት ሩሲያ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እንድታከብር አሳስቧል።

ፑቲን

የተጋነነ ዜና

አንድ ፌስቡክ ላይ የወጣ ጽሁፍ “ሩሲያ በተደጋጋሚ በክትባት ዓለምን ታድጋለች” ይላል።

የቀዝቃዛው ጦርነት የበሽታ ቁጥጥር የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ዶራ ቬራጋ አስተያየቱ “የተጋነነ” ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

ጽሁፉ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) እና የኮሌራ ክትባት ሩሲያ ውስጥ እንደተሠሩ ያትታል። ሆኖም ግን ዶሮ ላይ የሚሠራ የኮሌራን ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው ፈረንሳዊው ተመራማሪ ሉዊስ ፓስተር ነው።

ከዚያም እአአ 1885 ላይ ጄሚ ፈር የተባለ ስፔናዊ ሐኪም ሰዎችን ከበሽታው መከላከል እንዲቻል አደረገ።

ለልጅነት ልምሻ የመጀመሪያውን ውጤታማ ክትባት ያገኙት አሜሪካዊው የቫይረስ ተመራማሪ ዶ/ር ጆናስ ሳልክ ናቸው።

በመቀጠልም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የመጀመሪያው የልጅነት ልምሻ የጠብታ ክትባት የተገነ ሲሆን፤ እስካሁን ጥቅም ላይ የሚውለውም ይህ ክትባት ነው።

ክትባቱ የአሜሪካ እንዲሁም የሩሲያ (ሶቪየት) ጥምር ግኝት በመባል ይታወቃል።

ዶ/ር ዶራ እንደሚሉት፤ ክትባቱ የተሠራው በአሜሪካዊው ዶ/ር አልበርት ሳቢን እና በሶቪየቱ ሚኻይሊ ቾማኮቭ ጥምረት ነው።

የክትባቱ ዜና በሩ

ክትባቱ ከኮቪድ-19 ጋር የሚደረገውን ትግል ለማሸነፍ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ በሩሲያ ብሔራዊ ጣቢያ መገለጹ ይታወሳል።

ክትባቱ አስተማማኝ መሆኑ በብሔራዊው ቴሌቭዥን ከመገለጹ ባሻገር፤ ክትባቱ ‘ሱፑቲንክ’ ከተባለችው ሳተላይት ጋር እየተነጻጸረ ይገኛል።

ሳተላይቷ ሕዋ ላይ በማረፍ ግንባር ቀደሟ ናት።

ምዕራባውያን ክትባቱ ላይ ጥርጣሬ አለን ማለታቸውን ብሔራዊ ጣቢያው አጣጥሎታል። “ቅናት ነው” እንዲሁም “ሩስያ ላይ የተቃጣ የመረጃ ጦርነት ነው” ሲልም ምላሽ ሰጥቷል።

የዚህ ሳምንት የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ፤ ከ2016ቱ የኢቦላ ክትባት ዘገባ ጋር ይመሳሰላል።

ክትባቱ ሩሲያ ውስጥ መመዝገቡ፤ ለአገሪቱ የመድኃኒት አቅርቦት ዘርፍ ድል መሆኑ ተገልጾ ነበር። ማስረጃ ባይቀርብም ክትባቱ ከሩሲያ ውጪ ከተሠሩ ክትባቶች በበለጠ ውጤታማ መሆኑም ተገልጾ ነበር።

የፑቲን ልጅ ፎቶ ነው የተባለው ምስል
የምስሉ መግለጫ, የፑቲን ልጅ ፎቶ ነው የተባለው ምስል

መድኃኒት አምራቾች ላይ የተሰነዘረ ትችት

አንድ ከጣልያን የወጣ የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሁፍ፤ ፑቲንን በማጣቀስ የተጻፈ ነበር። በእርግጥ ጽሁፉ የሚያጣቅሰው ንግግር የሩሲያን መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የትም ቦታ አልተኘም።

ከ35 ሺህ ጊዜ በላይ በፌስቡክ የተሰራጨው ጽሁፉ፤ “መድኃኒት አምራቾች ክትባቱን እንድናዘገየው ጠይቀውናል። ይሄ የምጣኔ ሀብት ጉዳይ አይደለም። ሩሲያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ትታ ስለ ገንዘብ አታስብም" ይላል።

ጽሁፉ በፑቲን አድናቂዎች ገጽ ላይ የወጣ ጽሁፍ የተሳሳተ ትርጓሜ ሊሆን ይችላል።

በፑቲን ወዳጆች ገጽ ላይ መድኃኒት አምራቾችን የሚተችና ፕሬዘዳንቱን የሚያወድስ ጽሁፍ አለ።

በሁለቱም ጽሁፎች እንደተመለከተው፤ ሩሲያ ለክትባቱ በፍጥነት ፍቃድ የሰጠችው በመድኃኒት አምራቾች ተገፋፍታ ነው የሚል ትችት ሰፍሯል።

የሳይንቲስቶች ዋናው ስጋት ሩሲያ ስለ ክትባቱ አስተማማኝነት የሚያስረዳ ጽሁፍ አለማሳተሟ ነው።

ፑቲን ክትባቱን ልጃቸው እየወሰደች መሆኑን ተናግረዋል። ይህም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።

ፕሬዘዳንቱ የትኛዋ ልጃቸው ክትባቱን እንደወሰደች ይፋ ባያደርጉም፤ ክትባቱ ያስከተለው ብቸኛ የጎንዮሽ ጉዳት ተወሰነ ጊዜ መጠነኛ የሙቀት መጨመር መሆኑንም አብራርተዋል።

ሕንድ ውስጥ በስፋት የተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምስል፤ ክትባት ስትወስድ የምትታይ ሴት የፑቲን ልጅ እንደሆነች ይጠቁማል።

ወጣቷ የክትባት ምርምሩ አካል ብትሆንም፤ የፑቲን ልጅ ሳትሆን የወታደራዊ ሕክምና ተቋም ተማሪ ናት።

ሩሲያ አገኘሁት ያለችውን ክትባት በተመለከተ እነዚህና ሌሎችም ያልተረጋገጡ ዜናዎች፣ ምስሎችና ቪዲዮዎች በማኅበራዊው ሚዲያ መድረክ ላይ በስፋት እየተሰራጩ ነው።

ኮሮና
Banner