ኮሮናቫይረስ፡ ሐሰተኛ ዜና በሕንድ ያስከተለው ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሐሰተኛ ወይንም አሳሳች መረጃዎች በርካቶችን ግራ ከማጋባት አልፈው ከባድ ጉዳት ያስከትላሉ። በተለይ ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ብዙዎች በእንደዚህ አይነት መረጃዎች ተሳስተዋል። የዚህ ጉዳት ገፈት ቀማሽ ከሆኑት አገራት መካከል ሕንድ ተጠቃሽ ናት።
ይህም በሕንድ የሚገኙ በርካታ ታማኝና ትክክለኛ መረጃ የሚያደርሱ የዜና አውታሮች እንኳን ወረርሽኙን በተመለከተ ሥራቸውን በትክክል እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል።
አንዳንድ ትንሽ ቁጥር ያላቸው ማኅበረሰቦች፤ በተለይ ደግሞ የሥጋው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሕንድ ውስጥ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ነው።
ሕንድ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ጀምሮ ሐይማኖትን የተመለከቱ ነገሮች በበይነ መረብ ላይ ልዩ የመነጋገሪያና የበርካታ ሐሰተኛ መረጃዎች የሚወጡበት ጉዳይ ነው።
የቢቢሲ መረጃ ቡድን ባደረገው ማጣራት መሰረት በአምስት የሕንድ ድረገጾች ላይ 1447 መረጃዎች የተገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል 58 በመቶ የሚሆኑት ስለኮሮናቫይረስ የተሳሳተ አልያም ሐሰተኛ መረጃን የያዙ ናቸው።
አብዛኞቹ ደግሞ ኮሮናቫይረስ መድኃኒት ተገኘለት የሚሉና ኮሮናቫይረስ እንዴት እንደተነሳ ትክክለኛ መረጃ አለን የሚሉ ሰዎች የጻፏቸው ሀሳቦች ናቸው።
በአገሪቱ ኮሮናቫይረስ ብዙም ባልተሰራጨበት ከወርሃ ጥር ጀምሮ እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ውስጥ፤ ከሦስት የጎረቤት አገራት የሚመጡ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች የሕንድ ዜግነት ሊሰጣቸው ነው የሚል ዜና በስፋት ሲሰራጭ ነበር።
ምንም እንኳን ዜናው ሐሰተኛ ቢሆንም በሕንድ በርካቶች ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን እንዲገልጹ አድርጓል። ሙስሊሞችን የሚያገል ውሳኔ ነው በማለትም ብዙዎች ቁጣቸውን ገልጸው ነበር በወቅቱ።
በርካታ ሙስሊሞች በሚኖሩባት ሰሜን ምሥራቅ ዴልሂ ደግሞ ሕይወት እስከመጥፋት ያደረሰ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር።
በድረገጾቹ ላይ ከተለቀቁት መረጃዎች መካከል ሐሰተኛ ቪዲዮዎች፣ ከዚህ በፊት የተቀረጹ ቪዲዮዎችን እንደ አዲስ ማቅረብ፣ አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች፣ ሐሰተኛ ምስሎችና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ደግሞ በርካታ ሐሰተኛና አሳሳች መረጃዎች በሕንድ ተሰራጭተዋል።
በወቅቱ 'ታብሊጂ ጃማት’ የሚባል ኢስላማዊ ቡድን ያዘጋጀው ሐይማኖታዊ ዝግጅትን የታደሙ በርካታ ሙስሊሞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገልጾ ነበር።
ይህንን ተከትሎም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሕንዳውያን በቫይረሱ አለመያዝ ከፈለጉ ወደ ሙስሊሞች ሱቅ መሄድ እንዲያቆሙ መልዕክቶች በስፋት ይተላለፉ ነበር።
በርካታ ዝግጅቱን የታደሙ ተጨማሪ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለበቸው ሲገለጽ ደግሞ ነገሮች እየተባባሱ መጡ።
አትክልቶችን ይሸጥ የነበረው ኢምራን (ስሙ ተቀይሯል) ለቢቢሲ ሲገልጽ፤ በዋትስአፕ ይተላለፉ ከነበሩ መልዕክቶች ውስጥ አንድ ሙስሊም ነው የተባለ ሰው ዳቦዎች ላይ ምራቁን እየተፋ ለደንበኞቹ ሲሸጥ የሚያሳየው ሐሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስል ሙስሊሞች ላይ ከፍተኛ መገለል እንዲደርስ አድርጎ ነበር ይላል።
"አትክልቶችን ለመሸጥ ወደ መንደር ለመግባት ፈርተን ነበር’’ ይላል።
በዋና ከተማዋ ዴልሂ ደግሞ ሙስሊሞች ወደ መኖሪያ መንደሮችና ገበያ ማዕከላት መግባት እንደተከለከሉ አንድ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ለፖሊስ አስታውቆ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ሕንድ ውስጥ የተሰራጨው ሌላኛው መረጃ ሥጋን ከነጭራሹ አለመመገብና አትክልቶችን ብቻ መብላት ከኮሮናቫይረስ ይከላከላል የሚለው ነው።
የሕንድ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በመግባት ሐሰተኛ መረጃዎችን ሰዎችን እያሳሳቱ እንደሆነ ገልጾ ነበር።
በተለይ በዋትስአፕና በፌስቡክ ይተላላፉ የነበሩት ሐሰተኛ መረጃዎች ሙስሊሞችንና በሥጋ መሸጥ ላይ ሕይወታቸውን የመሰረቱ ሰዎችን ጎድቷል።
መንግሥት እንዳለውም ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የሥጋና የዶሮ ተዋጽኦ ዘርፉ ከሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ብቻ 1.4 ቢሊየን ፓውንድ ኪሳራ አጋጥሞታል።
በዚህ ዙሪያ ከተላለፉት ሐሰተኛ መረጃዎች መካከል የቀድሞው ታዋቂ የክሪኬት ተጫዋች ሳቺን ቴንዱልካር የሥጋ መሸጫ ሱቆች መዘጋት አለባቸው ብሎ ጠይቋል የሚለው ነው።
ከሐሰተኛ ዜናዎቹ በተጨማሪም ሰዎች በቆሎን የመሳሰሉ ጥራጥሬዎችን በብዛት መግዛት በመጀመራቸው ዶሮ አርቢዎች ዶሮዎቻቸውን የሚመግቡት በቆሎ እጥረት አጋጥሟቸው ነበር።
በዚህ ምክንያት ዴልሂ ውስጥ ብቻ የእንቁላል ሽያጭ 30 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ሙምባይ ውስጥ ደግሞ 21 በመቶ ቀንሷል። በቴላንጋና ግዛት ውስጥ በምትገኘው ሐይደርባድ ደግሞ የእንቁላል ሽያጭ 52 በመቶ አሽቆልቁሏል።


















