ኮሮናቫይረስን፡ በአዲሱ የሞባይል ቴክኖሎጂ ላይ የተነዛው ሐሰተኛ ወሬ ጉዳትን አስከተለ

ሞባይል ስልክ የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሞባይል ስልክ አገልግሎትን ፈጣንና ዘመናዊ ያደርገዋል ተብሎ የታመነበት የአምስተኛው ትውልድ [5ጂ] ቴክኖሎጂ የኮሮናቫይረስን እያሰራጨ ነው በሚል በተናፈሰው ወሬ ምክንያት በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው።

በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች በስፋት ሲዘዋወሩ በነበሩ ቪዲዮዎች ላይ እንደታየው ብሪታኒያ ውስጥ በሚገኙት በርሚንግሐምና መርሲሳይድ ከተሞች ውስጥ የሞባይል ግንኙነት ማማዎች በእሳት ሲጋዩ ታይተዋል።

ይህንን ተከትሎ የሴራ ንድፈ ሐሳብን በመመርኮዝ ዘመናዊው የአምስተኛው ትውልድ [5ጂ] ቴክኖሎጂ ለኮሮናቫይረስ መሰራጨት ምክንያት ሆኗል የሚለው ክስ በሳይንስ ባለሙያዎች ሐሰት ተብሎ ተወግዟል።

አዲሱ ቴክኖሎጂ በሽታውን እያስተላላፈ ነው የሚሉ መላምቶችን የያዙ መልዕክቶች ዕውቅና ባገኙና በመቶ ሺህዎች ተከታይ ባሏቸው የፌስቡክ፣ የዩቲዩብና የኢንስታግራም አካውቶች በኩል ሳይቀር በስፋት ሲሰራጩ ነበር።

ነገር ግን ሳይንቲስቶች ይህ በኮቪድ-19 እና በ5ጂ አገልግሎት መካከል አለ የተባለው ግንኙነት "ፍጹም የማይረባ" ከመሆኑ በተጨማሪ ከሥነ ፍጥረት እሳቤ አኳያም ሊሆን የማይችል ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

የሴራ ንድፈ ሐሳብን

የሬዲዮ ሞገዶችን በመጠቀም ለሞባይል ስልክ አገልግሎት የሚውለውን የ5ጂ ቴክኖሎጂ በስፋት እየተሰራጨ ላለው የኮሮናቫይረስ ተጠያቂ በማድረግ ይህንን ሐሰተኛ መረጃ በስፋት እያሰራጩ ያሉት ሰዎች የሴራ ንድፈ ሐሳብን መሰረት አድርገው ነው።

ይህ ወሬ መሰራጨት የጀመረው በጥር ወር መጨረሻ አካባቢ የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ታማሚ አሜሪካ ውስጥ በተገኘበት ሰሞን ሲሆን፤ ክስተቱ ከ5ጂ ጋር ግንኙነት እንዳለው በፌስቡክ በኩል ነበር ሲወራ የነበረው።

የሚሰራጨውም ወሬ ሁለት ገጽታ የነበረው ሲሆን አንደኛው 5ጂ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ አቅምን በመቀነስ ሰዎችን ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ያደርጋል የሚሉ ናቸው።

ሌሎቹ ደግሞ ቫይረሱ በቀጥታ በ5ጂ ቴክኖሎጂ በኩል ይተላለፋል ሲሉ ያልተረጋገጡ መልዕክቶችን በስፋት አሰራጭተዋል።

በሬዲንግ ዩኒቨርስቲ የሥነ ህይወት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክትር ሳይመን ክላርክ ግን እነዚህን ሁለት ሐሳቦች "ሙሉ ለሙሉ የማይረቡ" ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።

"5ጂ የሰዎችን በሽታን የመከላከል አቅም ይቀንሳል የሚለው ሐሳብም ለንግግር የሚበቃ አይደለም" ይላሉ ዶክተር ክላርክ።

"የተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅማችን በተለያዩ ምክንያቶች ዝቅ ሊል ይችላል፤ አንድቀን ሲደክመን ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥሩ ምግብ ሳናገኝ ስንቀር መዋዠቁ አይቀርም። ይህም ትልቅ ነው የሚባል ባይሆንም በቫይረሱ ለመያዝ ተጋላጭ ሊያደርግን ይችላል።

"በእርግጥ የራዲዮ ሞገዶች ጠንካራ በሚሆኑበት ጊዜ የሰውነታችን በሽታን የመከላከል ሥርዓት በአግባቡ ሥራውን ሊያከናውን አይችልም። ነገር ግን የ5ጂ የራዲዮ ሞገድ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ በሽታን የመከላከል ሥርዓታችንን ሊያስተጓጉል የሚችልበት አቅም የለውም። በዚህም ዙሪያ በርካታ ጥናቶች ተሰርተዋል።"

የሞባይል ኔትወርክ ማማ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የቫይረሱ ተፈጥሮና ባህሪይ

በብሪስቶል ዩኒቨርስቲ የህጻናት ህክምና ፕሪፌሰር የሆኑት አዳም ፊን እንደሚሉት ደግሞ የ5ጂ ቴክኖሎጂ ቫይረሱን ያስተላልፋል የሚባለው ነገር ፈጽሞ የማይሆን ነገር እንደሆነ ተናግረዋል።

"ኮሮናቫይረስ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፍ መሆኑ ይታወቃል። ቫይረስና ለሞባይል እንዲሁም ለኢንትርኔት ግንኙነት የሚያገለግለው ኤሌክትሮማግኔቲክ ሞገድ በአሰራራቸው የተለያዩ ነገሮች ናቸው" ብለዋል።

ከ5ጂ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የሚወራው ነገር ትክክል እንዳልሆነ እንደማሳያነት ከተጠቀሱት ምሳሌዎች መካከል፤ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የኮሮናቫይረስ በስፋት የተሰራጨባቸው ከተሞች ገና የ5ጂ አገልግሎትን ያላገኙ ናቸው።

በተጨማሪም በበሽታው ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢራን ቴክኖሎጂውን ሥራ ላይ ለማዋል ገና ጥረት እያደረገች ነው።

የ5ጂ ቴክኖሎጂን በተመለከተ የኮሮናቫይረስ ከመምጣቱ ቀደም ብሎ አንስቶ እጅግ አስፈሪ የሆኑ ነገሮች ሲወሩ ቆይተዋል። ከወራት በፊት ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት ከሞባይል ስልክ አማካይነት የሚከሰት የጤና ችግርን በተመለከተ ምንም አይነት ማስረጃ እንዳልተገኘ አመልክቷል።

የተለያዩ ተቋማትም በ5ጂ ቴክኖሎጂና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መካከል ግንኙነት አለ እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ "እንደሚያሳስባቸው" ገልጸው፤ እስካሁንም በሁለቱ መካከል ምንም አይነት የሚያሳምን ማስጃ እንዳልተገኘ ተገልጿል።

ቫይረሶች በተፈጥሯቸው የሰውን ወይም የእንስሳትን ህዋሳትን በመውረር ለመራባት ይጠቀሙባቸዋል፤ በዚህም ሳቢያ በሽታ ይከሰታል። ቫይረሶች ከሰውነት ውጪ ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ አይችሉም ለዚህም ነው በአብዛኛው በሳልና በማሽነጠስ ጊዜ በሚወጡ ፈሳሽ በሆኑና በጥቃቅን ብናኝ መልክ ወደ ሰውነት ለመግባት መንገድ የሚፈልጉት።

የዚህ የኮሮናቫይረስ ተፈጥሯዊ አወቃቀር እንደሚያመለክተው ቫይረሱ ከእንስሳት ወጥቶ ወደ ሰው የተሸጋገረ ሲሆን፤ ከዚያም ከሰው ወደ ሰው በመተላለፍ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

ኮሮና
Banner