ፌስቡክ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ሐሰተኛ መረጃዎችን ሊጠቁም ነው

ስልክ የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፌስቡክ ኮሮናቫይረስን በተመለከተ በርካታ ሐሰተኛ መረጃዎች ይተላለፉበታል

ስለኮሮናቫይረስ ሐሰተኛ መረጃ ያነበቡ፣ የተመለከቱ እንዲሁም መረጃውን ለሌላ ሰው ያጋሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ሊላክላቸው መሆኑን ፌስቡክ አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን "infodemic" የሚል መጠሪያ ሰጥቷቸዋል። ፌስቡክም የእነዚህን ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭትን ለመግታት ሲል አዲሱን አሠራር ተግባራዊ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።

አንድ ገለልተኛ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ከወረርሽኙ ጋር የተያያዙ ሐሰተኛ መረጃዎች በዋናነት የሚሰራጩት በፌስቡክ ነው። በተለይ በስፓኒሽ ቋንቋ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ፌስቡክ በበኩሉ ጥናቱ ድርጅቱ አሁን የሚገኝበትን ደረጃ አያሳይም ይላል።

መቀመጫውን ካሊፎርንያ ያደረገው ድርጅት፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት ማስጠንቀቂያውን በዜና ገፆች ላይ ማስተላለፍ ይጀምራል።

ማስጠንቀቂያው ተጠቃሚዎች ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ወደ ዓለም የጤና ድርጅት ገፅ ይመራል።

የፌስቡክ አርማ

ሐሰተኛ መረጃን መለየት

የፌስቡክ ቃል አቀባይ እንደሚሉት፤ ስለ ቫይረሱ ሐሰተኛ መረጃ ደርሷቸው፣ ከዚያም ትክክለኛ አለመሆኑን የደረሱበት ሰዎች መረጃውን ከፌስቡክ ውጪ ቢያገኙት እርስ በእርስ መረጃ የሚለዋወጡበት መንገድ ተዘርግቷል።

ፌስቡክ አዲሱን አሠራር የዘረጋው ከሐሰተኛ መረጃ ጋር ተያይዞ በስድት ቋንቋዎች የተሠራ ጥናትን ተከትሎ ነው። ጥናቱን የሠራው ‘አቫዝ’ በተባለ የመብት ተሟጋች ቡድን ነው።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ያለ ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከወረርሽኙ ጋር ለተያያዙ ሐሰተኛ መረጃዎች እየተጋለጡ መሆኑን አጥኚዎች ይናገራሉ።

አጥኚዎቹ ከደረሱባቸው ሐሰተኛ መረጃዎች መካከል፤ ኮሮናቫይረስ ጥቁሮችን አይዝም የሚለው እና ክሎሪን ዳይኢክሳይድ ቫይረሱን ይገድለዋል የሚሉት ይገኙበታል። እነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ደርሰዋል።

‘አቫዝ’ የተባለው ቡድን በእንግሊዘኛ፣ በስፓኒሽ፣ በፖርቹጋልኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ከተሰራጩ 100 መረጃዎች ናሙና ወስዷል።

እነዚህን ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ፈትሾም ቀጣዩን ውጤት አግኝቷል።

1. የፌስቡክ አጋር ድርጅቶች ወይም ሌላ አካል አንድ መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ለፌስቡክ ከጠቆመ በኋላ፤ ፌስቡክ ስለመረጃው ሐሰተኛን ማስጠንቀቂያ ለመጻፍ እስከ 22 ቀን ድረስ ሊወስድ ይችላል።

2. በእንግሊዘኛ ከተጻፉ ሐሰተኛ መረጃዎች 29 በመቶ የሚሆኑት፤ የተሳሳቱ ስለመሆናቸው የሚጠቁም ማስጠነቀቂያ አልነበራቸውም።

3. 70 በመቶ የሚሆኑት የስፓኒሽ ሐሰተኛ መረጃዎች፣ 68 በመቶ የሚሆኑት የጣልያንኛ ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲሁም 50 በመቶ የሚሆኑት የፖርቹጋልኛ ሐሰተኛ መረጃዎች፤ የተሰሳቱ ስለመሆናቸው የሚጠቁም ማስጠንቀቂያ አልነበራቸውም።

4. በአረብኛ ከተጻፉት ሐሰተኛ መረጃዎች ማስጠንቀቂያ ያልነበራቻው 22 በመቶው ናቸው።

ፌስቡክ እንደሚለው፤ በተለያየ ቋንቋ የሚሠሩ እውነተኛ መረጃን ከሐሰተኛው የሚለዩ ባለሙያዎች መቅጠሩን ገፍቶበታል። ከታማኝ ድርጅቶች ጋር በመጣመርና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በ50 ቋንቋዎች የሚሠሩ ባለሙያዎች መቅጠሩንም ድርጅቱ ያክላል።

የ‘አቫዝ’ ንቅናቄ ዳይሬክተር ፋዲ ቁርዓን ግን “ስለ ወረርሽኙ ሐሰተኛ መረጃ በዋነኛነት የሚሰራጨው በፌስቡክ ነው” ይላሉ።

ድርጅቱ ሐሰተኛ መረጃን ለተጠቃሚዎች ለመጠቆም መወሰኑን እንደ ትልቅ እርምጃ ያዩታል።

“ፌስቡክ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማጽዳት ሁነኛ ውሳኔ ላይ ደርሷል። ተጠቃሚዎችን የሐሰተኛ መረጃ ጥቆማ በመስጠትና ሕይወታቸውን ወደሚታደግ ትክክለኛ መረጃ በመጠቆም ግንባር ቀደቡ ማኅበራዊ ሚዲያ ይሆናል።”

የፌስቡክ መልዕክት

የፎቶው ባለመብት, Facebook

የምስሉ መግለጫ, ስለኮሮናቫይረስ የሚወጡ ሐሰተኛ መረጃዎች በስፋት ይሰራጫሉ

ሐሰተኛ መረጃን በመግታት ሕይወት ማዳን

ከተሰራጩት ሐሰተኛ መረጃዎች አንዱ፤ ሰዎች ብዙ ውሃ በመጠጣት፣ በጨውና በዝንጅብል በመጉሞጥሞጥ ራሳቸውን ከቫይረሱ መከላከል ይችላሉ የሚለው ነው።

ይህንን መረጃ ተጠቃሚዎች ከ 31 ሺህ ጊዜ በላይ ተጋርተውታል። አቫዝ ይህንን ሐሰተኛ መረጃ ለፌስቡክ ከጠቆመ በኋላ ድርጅቱ መረጃውን ከገፁ አውርዶታል።

ሆኖም ግን አሁንም 2,600 የሚሆኑ የመረጃው ግልባጮች ድረ ገፅ ላይ ይገኛሉ። መረጃው ያለ ፌስቡክ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ወደ 100 ሺህ ጊዜ ተሰራጭቷል።

የፌስቡክ መስራችና ዋና ኃላፊ ማርክ ዙከርበርግ፤ በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ላይ ሁለት ቢሊዮን ተጠቃሚዎችን ወደ ትክክለኛ መረጃ መርተናል ሲል ድርጅቱን ተከላክሏል።

350 ሚሊዮን ሰዎች ስለ ቫይረሱ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት እንደተጠቀሙበትም ይናገራል።

“አካላዊ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ሐሰተኛ መረጃን እናስቆማለን፤ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ ከበሽታው አይከላከልም የሚሉና ሌሎችም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሐሰተኛ መረጃዎችን ከገፃችን አውርደናል” ሲልም ያስረዳል።

ማርክ እንደሚለው፤ 95 በመቶ የሚሆኑት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች፤ የሐሰተኛ መረጃ ጥቆማ ሲደርሳቸው፤ መረጃውን ከማንበብ ወይም ከመመልከት ይቆጠባሉ።

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያጠኑት ባለሙያ ኤምሊ ቴይለር፤ ፌስቡክ ጥሩ እርምጃ ወስዷል ይላሉ። በተለይም በቀደመው የአሜሪካ ምርጫ ወቅት ከተወሰደው እርምጃ ጋር እንዲህ ያነጻጽሩታል።

“ጉልህ ለውጥ ያምጣ አያምጣ አናውቅም፤ ነገር ግን መሞከር አለበት። በምርጫ ወቅት የሚሰራጭ ሐሰተኛ መረጃ እና ከጤና ጋር የተያያዘ ሐሰተኛ መረጃ መካከል ልዩነት አለ። ጤና ነክ ሐሰተኛ መረጃ የሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል።”

ኮሮና
Banner