ልዑል አልጋ ወራሹ የማይወጧቸው ሦስት ፈተናዎች

ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን

አሁን ያለንበት ወቅት ለሳዑዲ መንግሥት በተለይ ደግሞ ለልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ምቾት የሚፈጥር አይደለም።

ምንም እንኳ ኤምቢኤስ በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ልዑል አልጋ ወራሽ በአገራቸው ዜጎች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እንዳለ ቢሆንም፤ በዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ በጎ ገጽታቸውን የሚያጠለሹ ክስተቶች መኖራቸው አልቀረም።

ከሁለት ዓመት በፊት ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ የጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ መገደል ዓለም ኤምቢኤስን በጥርጣሬ እንዲያያቸው ምክንያት ሆኗል።

አሁን ላይ በአሜሪካ አዲስ ፕሬዝደንት መመረጡ የልዑሉ ሌላኛው ራስ ምታት ነው።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶ ባይደን ገና ከአሁኑ አስተዳደራቸው በሳኡዲ አረቢያ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያለ አቋም እንደሚይዝ አስታውቀዋል።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሦስት ጉዳዮች በዋሽንግተን እና ሪያድ ወዳጅነት መካከል ነፋስ የሚያስገቡ ለሆኑ ይችላሉ። በቀጣይም የኤምቢኤስ ፈተናዎች ሆነው መዝለቃቸው አይቀርም።

2px presentational grey line

የየመን ጦርነት

የየመን ጦርነት በጦርነቱ ለተሳተፉት ሁሉ መዘዝን ይዞ መጥቷል። ካልተገመተ ፈተና ውስጥም ከቷቸዋል።

ሳኡዲ አረቢያ ጦርነቱን አልጀመረችውም። የየመንን የእስር በእርስ ጦርነት ያስጀመሩት ሁቲዎች ናቸው። እአአ 2014 ላይ የሁቲ አማጺያን ወደ የመን መዲና ሰነዓ ዘምተው ሕጋዊ መሠረት ያለውን መንግሥት ከጣሉ በኋላ አገሪቷን ወደ የእርስ በእስር ጦርነት አስገብተዋል።

ሁቲዎች በየመን ሰሜናዊ ተራራማ ቦታ በስፋት የሚኖሩ ሲሆን ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ 15 በመቶውን ይወክላሉ።

እአአ ሕዳር 2015 ላይ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ሁቲዎችን ለመዋጋት የአረብ አገራትን ማስተባበር ያዙ።

ልዑል አልጋ ወራሹ የበርካታ አረብ አገራትን የተባበረ ክንድ በማስተባበር በአየር ጥቃቶች የሁቲ አማጺያንን በጥቂት ወራት ውስጥ ማንበርከክን ዓላማ አድርገው ነበር የተነሱት።

በጥቂት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው የጦር ኦፕሬሽን ግን ስድስት ዓመታት አስቆጥሮም መገባደጃው አልታወቀም።

ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ተገድለዋል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በሁለቱም ጎራ የሚፋለሙት ኃይሎች የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል።

አሁንም ሳኡዲ መራሹ ኃይል የሁቲ አማጺያንን ከሰነዓ እና የበርካቶች መኖሪያ ከሆነው ምዕራብ የመን ማስወጣት አልተቻለውም።

በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን የሚያስወነጭፏቸው ዒላማቸውን የጠበቁት ሚሳኤሎች እንዲሁም የድሮን ጥቃቶች የሳኡዲ አረቢያን ነዳጅ ማብላያ ጣቢያን በመምታት በሳኡዲ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረስ ችለዋል።

ሳኡዲ መራሹ ኃይል የሁቲ አማጺያንን ከሰነዓ ማስወጣት ተስኖት ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሳኡዲ መራሹ ኃይል የሁቲ አማጺያንን ከሰነዓ ማስወጣት ተስኖት ቆይቷል።

ሳኡዲ አረቢያ ራሷን ከዚህ ጦርነት ለማውጣት ጽኑ ፍላጎት አላት። የሁቲ ታጣቂዎች ሰነዓን እንደተቆጣጠሩ ከጦርነቱ መውጣት ግን ለሳኡዲ የማይሆን አማራጭ ነው።

የሁቲ አማጺያን በስልጣን ላይ እንዲቆዩ መፍቀድ ማለት ኢራን በየመን ጠንካራ መሠረት እንዲኖራት መፍቀድ ማለት ነው። ይህን ደግሞ እንዲሆን ሳኡዲ ትፈቅዳለች ተብሎ አይጠበቅም።

ሪያድ በየመን የእስር በእርስ ጦርነት በነበራት ተሳትፎ ከትራምፕ አስተዳደር የጠየቀችውን ድጋፍ ስታገኝ ቆይታለች። ይህ ድጋፋ ግን በባይደን አስተዳደር የሚቀጥል አይሆንም።

ለኤምቢኤስ ጦርነቱን ጥሎ መውጣት አማራጭ አይደለም። ባካሄዱት የጦር ኦፕሬሽንም የጠበቁትን ድል ማምጣት ተስኗቸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኃያሏ አሜሪካን ድጋፍ የማግኘታቸው ጉዳይ ጥያቄ ላይ ወድቋል።

2px presentational grey line

በእስር የሚገኙ የሳዑዲ ሴቶች

የመብት ተሟጋች ሴቶች እስር የሞሐመድ ቢን ሰልማን አስተዳደር በበጎ እንዳይታይ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው።

13 ጠንካራ የሳኡዲ አረቢያ የመብት ተሟጋቾች ለእስር ከተዳረጉ ሰንበትበት ብለዋል። ሴቶቹ የታሰሩባቸው ምክንያቶች ደግሞ መኪና ማሽከርከራቸው እና የወንድ ፍቃድ ማግኘት የለብንም በሚል ድምጻቸውን ማሰማታቸው ነው።

እንደ ሉወጄይን አል-ሃታሎለ ያሉ የመብት ተከራካሪዎች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ። የሳኡዲ መንግሥት ሉወጄይን ከውጪ ኃይሎች ገንዘብ ተቀብላለች ሲሉ ይከሰቷል። ለዚህ ግን አሁንም ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም።

ጓደኞቿ ግን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮንፍረንስ ላይ ከመሳተፏ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለመቀጠር የሥራ ማመልከቻ ከማቅረቧ ውጪ ያደረገችው ምንም የለም ይላሉ።

ሉወጄይን አል-ሃታሎለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሉወጄይን አል-ሃታሎለ

የመብት ተከራካዊዎቹ እስር በባይደን አስተዳደር እንዲሁ በዋዛ የሚታለፍ አይሆንም።

የቢቢሲው የመካከለኛው ምስራቅ ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር፤ ምናልባትም የሳኡዲ መንግሥት ለዓመታት አስሮ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ፤ "ምህረት አድርጊያለሁ" በማለት የመብት ተሟጋች ሴቶቹን ከእስር ሊለቅ ይችላል ይላል።

2px presentational grey line

ኳታርን የማግለል ሴራ

ኳታር በጎረቤት አገራት ተገላ ቆይታለች። ኳታር እንድትገለል ሴራውን ከጠነሰሱት መካከል ደግሞ ሳኡዲ ቀዳሚዋ ናት። ኩዌት ግን ችግሩን ለመፍታት ከመጋረጃው ጀርባ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። ይህ ግን በቀላሉ የሚፈታ ላይሆን ይችላል።

እአአ 2017 ላይ ፕሬዝደንት ትራምፕ በሪያድ ጉብኝት ባደረጉ በቀናት ልዩነት፤ ሳኡዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ባህሬን እና ግብጽ ተባብረው የባህረ ሰላጤ ጎረቤት አገራቸው ኳታርን አገለሉ።

ለዚህም ምክንያታቸው ኳታር ለጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኖች ድጋፍ ታደርጋለች የሚል ነው። ይህም ከሽብር ይመደባል ይላሉ።

ትራምፕ፣ አልሲሲ እና ንጉሱ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ዩናይድ አረብ ኤሜሬትስ መኖሪያቸውን ኳታር ያደረጉ ናቸው ያለቻቸውን የአሸባሪዎች ዝርዝር አቅረባ ነበር።

አገራቱ ኳታር ሽብርተኞችን መደገፏን ማቆም አለባት፣ የቱርክ ወታደሮች ከኳታር መውጣት አለባቸው፣ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ታቁም ከሚለው ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች በተጨማሪ የኳታሩ አልጀዚራ ይዘጋ የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቷት ነበር።

ይህ ተፈጻሚ ካልሆነ ኳታር ላይ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች እንጥላለን ሲሉም አስጠነቀቁ።

ልክ የሳኡዲ መራሹ ኃይል በየመን ጦርነት በወራት ውስጥ የተፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል የሚለው የተሳሳተ ስሌቱ በኳታርም ተደግሟል።

አገራቱ አንድ ላይ በማበር ኳታርን ሲያገሉ፤ ኳታር ጫናውን መቋቋም ተስኗት እጅ መስጠቷ አይቀርም የሚል መላምት ይዘው ነበር የተነሱት። ይህ ግን አልሆነም።

ኳታር ባላት የተፈጥሮ ሃብት፣ በዩናይትድ ኪንግደም ያላት ኢንቨስትመንት እንዲሁም ከቱርክ እና ኢራን ያገኘቻቸው ድጋፎች የአረብ አገረቱ ያሰቡት እንዳይሳካ ረድቷታል።

በቅርብ ዓመታትም በመካከለኛው ምስራቅ ሁለት ጎራ ተፈጥሯል።

የሱኒ ባህረ ሰላጤ አገራት ሳኡዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ባህሬን ከግብጽ ጋር በአንድ ጎራ ሲሰለፉ፤ ኳታር፣ ቱርክ እና እንደ ሙስሊም ብራዘርሁድ እና ሃማስ የመሳሰሉ በርካታ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎች በሌላኛው ጎራ ተሰልፈዋል።

የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ጃሬድ ኩሽነር በባህረ ሰላጤው አገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በድርድር ለመፍታት ወደ አገራቱ ተጉዘው ነበር።

አሜሪካ በኳታር ግዙፍ ወታደራዊ ካምፕ እንዳላት ሁሉ መጪው የባይደን አስተዳደርም ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረጉ አይቀርም።