ሳዑዲ አረቢያ፡ የውጭ አገር ዜጋ ጥንዶች ሆቴል እንዲከራዩ ተፈቀደ

በታሪካዊቷ ከተማ ዲሪያህ ሕንፃ አንድ ሳዑዲ አረቢያዊ ግለሰብ ሲራመድ የሚያሳይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሳዑዲ አረቢያ ለጎብኝዎች ሳቢ ለመሆን ሕጎቿን እያለዘበች ነው።

የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ወደ አገሪቷ የሚመጡና ያልተጋቡ የውጭ አገር ዜጋ ጥንዶች ሆቴል ተከራይተው አንድ ላይ ማሳለፍ እንደሚችሉ ገለፀ።

ይህ የሆነው በአገሪቷ የወጣውን አዲሱን የቪዛ ሕግ ተከትሎ ሲሆን ሕጉ የሳዑዲ አረቢያ ሴቶች በሆቴል ውስጥ ብቻቸውን ማሳለፍ እንደሚችሉም ይፈቅዳል። ከዚህ ቀደም ጥንዶች በሆቴል ለማሳለፍ በጋብቻ የተሳሰሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸው ነበር።

የሕጉ መሻሻል የአገሪቷ መንግሥት ጎብኝዎችን ለመሳብ የወሰደው እርምጃ ነው ተብሏል።

ከዚህ ቀደም ጥንዶች በጋብቻ መተሳሰራቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ ካላቀረቡ ሆቴል መከራየት እንደማይችሉ የሚከለክለው ሕግ አሁን ላይ ለውጭ አገር ዜጎች ተፈቅዷል።

የአገሪቷ የቱሪዝምና ብሔራዊ ቅርስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ "ማንኛውም የሳዑዲ ዜጋ ሆቴል ለመከራየት የቤተሰብ መታወቂያ አሊያም የግንኙነታቸውን ሁኔታ ማረጋጋጫ እንዲያሳዩ ይጠየቃሉ" ይላል።

ይሁን እንጂ ይህ ሕግ ከውጭ አገር ለሚመጡ ጎብኝዎች፣ የሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን ጨምሮ ሁሉም ሴቶች መታወቂያ በማሳየት ብቻ ሆቴል መከራየትና በክፍሎቹ በነፃነት ማሳለፍ እንዲችሉ ይፈቅዳል።

አዲሱ የቪዛ ሕግ እንደሚያትተው የውጭ አገር ሴት ጎብኝዎች በአለባበሳቸው ሙሉ በሙሉ እንዲሸፈኑ ባይገደዱም የሰውነት ክፍላቸውን የማያጋልጥ እንዲለብሱም ያዛል።

የአልኮል መጠጦች መጠጣት ግን የተከለከለ ነው።

በ'ኢንድፔንደንት' ጋዜጣ ኤዲተር የሆኑት ሳይመን ካልደር የቪዛ የሕጉ መሻሻል ወደ አገሪቷ የሚገቡ ጎብኝዎችን ቁጥር ሊያሳድገው ይችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በዓለማችን ሃብታም ከሆኑት አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሳዑዲ አገሪቷን ለጎብኝዎችና ለባለሃብቶች ምቹ ለማድረግ ሕጎቿን እያለዘበች ትገኛለች።

ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በቅርቡ ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩና ያለምንም ጠባቂ ሴቶች ከአገር ውጭ ጉዞ እንዲያደርጉ የሚያዘውን ሕግ ጨምሮ በጣም የከረሩ ሕጎች ላይ የተወሰነ ማሻሻያ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ሳዑዲ አረቢያ ከጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጅ ግድያ ጋር በተገናኘ አሁንም ገፅታቸው እንደጠለሸ ነው።