ሳዑዲ አረቢያ የጀማል ኻሾግጂን ግድያ መረጃ ለማጥፋት ባለሙያዎች ልካለች

ጀማል ኻሾግጂ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የዋሽንግተን ፖስቱ አምደኛ እንደወጣ የቀረው ጥቅምት 2 ነበር

ከፍተኛ የቱርክ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ጀማል ኻሾግጂ ከተገደለ በኋላ ሳዑዲ አረቢያ የኬሚካል እና የቶክሲኮሎጂ ባለሙያዎችን ኢስታንቡል ወደሚገኘው ቆንጽላዋ ልካለች።

ሳዑዲ፤ ጋዜጠኛ ጀማል ባሳለፍነው ወር በሳዑዲ ቆንጽላ ውስጥ መገደሉን ብታምንም ስለ አሟሟቱ እርስ በእርስ የሚጣረሱ መረጃዎችን ስትሰጥ ነበር።

የቱርክ መርማሪዎች ኻሾግጂ ታንቆ እንደተገደለ እንዲሁም አስክሬኑ በኬሚካል እንዲቀልጥና እንዲተን መደረጉን ያምናሉ።

ከሁለት ቀናት በፊት ሁለት የጀማል ኻሾግጂ ልጆች ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ የአባታቸው አስክሬን እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል።

''አሁን የምንሻው አባታችንን በመዲና ከተማ አል-ባቂ መቃብር ስፍራ ቤተሰቦቹ በተቀበሩበት ስፍራ ግብዓተ መሬቱን መፈጸም ነው'' በማለት ሳላህ ኻሾግጂ ተናግሯል።

''በጉዳዩ ላይ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር መክረናል። ጥያቄያችንን ይቀበላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ'' ብሏል።

ኻሾግጂ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ቱርክ በሚገኘው የሳዑዲ ቆንጽላ ውስጥ ጋብቻ ለመፈጸም የሚረዳውን ሰነድ ለማግኘት በሄደበት ወቅት ነበር የተገደለው።

ቱርክ ተፈጽሟል የምትለው ምንድነው?

የቱርክ ባለስልጣናት፤ ጀማል ኻሾግጂ በሳዑዲ አረቢያ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት ውስጥ ከተገደለ በኋላ የሳዑዲ ባለስልጣናት የኬሚካል ባለሙያ የሆነ አብዱላዚዝ አለጃኖቢ እና የቶክሲኮሎጂ ባለሙያ የሆነ ካሊድ ያይሃ አል-ዛሀረን የተባሉ ግለሰቦችን በመላክ ከግድያው ጋር የተያያዙ መረጃዎች እንዲያጠፉ አድርጋለች ይላሉ።

አንድ የቱርክ ጋዜጣ፤ ሁለቱ ግለሰቦች ጀማል ኻሾግጂ ከተገደለ ከአስር ቀናት በኋላ ወደ ቱርክ እንደሄዱና ለአምስት ቀናት ተልዕኳቸውን ለመፈጸም እንደቆዩ፤ ከዚያም ለሶስት ቀናት በቱርክ ቆይታ አድርገው ወደ ሳዑዲ እንደተመለሱ አስነብቧል።

የሳዑዲ ምላሽ

ጀማል ኻሾግጂ ከተሰወረ በኋላ በሳዑዲ መንግሥት ሲሰጥ የነበረው ምላሽ የሚጣረስ ሆኖ ቆይቷል።

በወቅቱ የቱርክ ባለስልጣናት በሳዑዲ ሰዎች ስለመገደሉ የድምጽ ማስረጃ አለን ያሉ ቢሆንም ሳዑዲ ግን በተደጋጋሚ ጀማል ወደ ቆንጽላው ከገባ ከደቂቃዎች በኋላ ቆንጽላውን ለቆ ወጥቷል ስትል ቆይታለች።

ሳዑዲ ጀማል ከተሰወረ ከቀናት በኋላ ደግሞ መገደሉን አምናለች።

ሳዑዲ መገደሉን ከማመኗ በፊት፤ የሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ በቆንጽላው ውስጥ በነበሩ ሰዎች እና በጀማል መካከል በተፈጠረ ጸብ ምክንያት ሊሞት ችሏል ብላ ነበር።

ጀማል ኻሾጂ ማን ነበር?

ጀማል ኻሾግጂ በሳዑዲ ዝነኛ ጋዜጠኛ ነበር። የሶቪየት ሕብረት የአፍጋኒስታን ወረራን በዝርዝር ዘግቧል። እንደ ኦሳማ ቢን ላደን ላሉ ግለሰቦች ቃለ መጠይቅ አድርጓል።

ለበርካታ አሰርት ዓመታት ለሳዑዲ ንጉሳውያን ቤተሰብ የቅርብ ሰው የነበረ ሲሆን፤ የሳዑዲ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን አማካሪ ሆኖም ሰርቷል።

ባለፈው ዓመት ግን ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሃገር ጥሎ ወደ አሜሪካ ተሰደደ። አሜሪካ ሳለ የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ ነበር። በጽሑፎቹ የሳዑዲ አረቢያውን ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ይተች ነበር።

ይህ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ እንዳስገባው በርካቶች ይናገራሉ።