በአስገዳይነት የሚጠረጠሩት የሳዑዲው ልዑል፣ የኻሾግጂን ገዳዮች ለፍርድ እንደሚያቀርቡ ዛቱ

አባቱን አስገድለዋል የሚባሉት ልዑሉ የሟችን ልጅ፥ ሳላህ ቢን ኻሾግጂን አስጠርተው ሲያጽናኑት የሚያሳየው ምስል ቁጣን ቀስቅሷል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, አባቱን አስገድለዋል የሚባሉት ልዑሉ የሟችን ልጅ፥ ሳላህ ቢን ኻሾግጂን አስጠርተው ሲያጽናኑት የሚያሳየው ምስል ቁጣን ቀስቅሷል

ሳዑዲ አረቢያን ሰቅዞ የያዘው የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ጉዳይ በሦስተኛ ሳምንቱም ዓለምን ማነጋገሩ አላበቃም።

ከሕዝብ ዕይታ ጠፍተው የከረሙት የሳኡዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን "የበረሃው ዳቮስ" በሚሰኘው የሪያድ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ ብቅ ብለው ንግግር አድርገዋል።

"እኔን አያድርገኝ፤ ጥፋተኞችን ካልቀጣሁ" ሲሉም ዝተዋል።

"ይህ ወንጀል ሳኡዳዊያን አንገት ያስደፋ ነው" ያሉት ልዑሉ በጋዜጠኛው ግድያ እጃቸውን ያስገቡ ሁሉ የስራቸውን ያገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ የተነሳ ግን ከቱርክ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሊሻክር እንደማይገባም አስገንዝበዋል።

ጋዜጠኛው እንዲገደል ትዕዛዝ ሰጥተዋል የሚባሉት ልዑል ባለፉት ቀናት የሟቹን ልጅ ሳላሕ ቢን ኻሹግጂን ወደ እልፍኛቸው አስጠርተው አጽናንተውታል።

ይህንኑ የሚያሳየው ምሥል ከቀረበ ወዲህ ብዙዎች ቁጣቸውን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሲገልጹ ነበር።

ሳዑድ አረቢያ በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ጉዳይ ዙርያ እርስ በርሱ የሚጣረስ መረጃን ለዓለም ስታቀብል ሰንብታለች።

ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ልዑሉ ሳያውቁት ይህ ወንጀል ሊፈጸም ይችላል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው

በመጀመርያዎቹ ቀናት ጋዜጠኛው ጀማል ቆንጽላችን ከገባ በኋላ በጓሮ በር ሾልኮ ወጥቷል ስትል የነበረችው ሳዑዲ አፍታም ሳትቆይ ጋዜጠኛው በኤምባሲዋ ውስጥ መገደሉን አምናለች። ኾኖም ከደህንነት ሰዎች ጋር አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ ገብቶ ቡጢ አርፎበት ነው የሞተው ብላ ነበር።

ጣኢብ ራሲብ ኤርዶዋን ከትናንት በስቲያ ሸንጎ ቀርበው ባደረጉት ንግግር ሳኡዲዎችን "የሻኾግጂን ሬሳ የት አደረሳችሁት?" ሲሉ ጠይቀዋቸዋል።

አንካራ ቀስ በቀስ ለመገናኛ ብዙኃን ያሾለከቻቸው መረጃዎች የሳኡዲ ንጉሣዊ ቤተሰብ በወንጀሉ ስለመሳተፉ የሚጠቁሙ ኾነዋል።

የአሜሪካ የስለላ መሥሪያ ቤት ኃላፊም ዘለግ ላለ ሰዓት በቱርክ ቆይታ እንዳደረጉና ምናልባትም ቱርክ ጋዜጠኛው በአሰቃቂ ሁኔታ ስለመገደሉ ያስረዳሉ ያለቻቸውን የድምጽ መረጃዎች እንዲያዳምጡ እንዳደረገቻቸው ይገመታል።

ግድያውን ተከትሎ የሪያዱ የኢንቨስትምነት ጉባኤ ስመ ጥር የሆኑ ባለሐብቶችና ርዕሰ ብሔሮች ላለመገኘት ወስነዋል።

የኢፌድሪው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጉባኤውን ለመታደም ከቀናት በፊት ወደ ሪያድ ማምራታቸው ይታወሳል።