ስለ ሳዑዲው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ አሟሟት እስካሁን የምናውቀው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሳዑዲ ዜግነት ያለው ዝነኛው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ ቱርክ ኢስታንቡል ወደ ሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ገብቶ ደብዛው ከጠፋ ሁለት ሳምንታት አልፈው ነበር።
በወቅቱ የቱርክ ባለስልጣናት በሳዑዲ ሰዎች ስለመገደሉ የድምጽ ማስረጃ አለን ብለዋል ።
ሳዑዲ ግን በተደጋጋሚ ጀማል ወደ ቆንስላው ከገባ ከደቂቃዎች በኋላ ቆንስላውን ለቅቆ ወጥቷል ብትልም አሁን ግን መገደሉን አምናለች።
ሳዑዲ ጀማል መገደሉን ከማመኗ በፊት የሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ በቆንስላው ውስጥ በነበሩ ሰዎች እና ጀማል መካከል በተፈጠረ ጸብ ምክንያት ሊሞት ችሏል ብለው ነበር።
ስለ ጀማል ኻሾጂ አሟሟት እስካሁን የምናውቃቸው እውነታዎች የሚከተሉት ናቸው።
ጀማል ኻሾጂ ማን ነበር?
ጀማል በሳዑዲ ዝነኛ ጋዜጠኛ ነበር፤ የሶቪየት ሕብረት የአፍጋኒስታን ወረራን በዝርዝር ዘግቧል። እንደ ኦሳማ ቢን ላድን ከመሳሰሉ ግለሰቦች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል።
ለበርካታ አስርት ዓመታት ለሳዑዲ ንጉሳውያን ቤተሰብ የቅርብ ሰው ነበር፤ የሳዑዲ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን አማካሪ ሆኖም ሰርቷል።
ባለፈው ዓመት ግን ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሃገር ጥሎ ወደ አሜሪካ ተሰደደ። አሜሪካም ሆኖ የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ ሆነ። በጽሑፎቹ የሳዑዲ አረቢያውን ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማንን ይተች ነበር።
ይህን ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ እንዳስገባው በርካቶች ይናገራሉ።
ወደ ሳዑዲ ቆንስላ ለምን አቀና?
ጀማል ወደ ቆንስላው የሄደው ከቀድሞ ሚስቱ ጋር መፋታቱ የሚያረጋገጥ ዶሴ ለማግኘት፣ ከዚያም ቱርካዊት እጮኛውን ለማግባት በእለተ አርብ ሴብቴምበር 28 በቆንስላው ተገኘ።
በቆንስላው ያሉ ሰዎች ግን ለማክሰኞ ኦክቶበር 2 ቀጠሩት።
''ቱርክ ውስጥ በሚገኝ የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ ምንም ሊያደርጉኝ አይችሉም ብሎ ገምቶ ነበር'' ስትል እጮኛው ለዋሽንግተን ፖስት ጽፋለች።
''ጀማል ምንም እንደማይገጥመው እርግጠኛ ነበር''
ማክሰኞ ሴብቴምበር 2 ከቀጠሮ ሰዓት 15 ደቂቃ ቀደም ብሎ ወደ ቆንስላው ሲገባ በተንቀሳቃሽ ምስል ይታያል።
ጀማል ወደ ቆንስላው ከመግባቱ በፊት ለእጮኛው ሁለት ስልክ ቁጥሮች ሰጥቷት ካልተመለስኩ ለቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይር ኤርዶጋን አማካሪዎች ደውለሽ ንገሪያቸው ብሏት ነበር።
እጮኛው ሳትታክት ለ10 ስዓታት በቆንስላው በር ላይ ጠበቀችው። በነጋታውም ወደ ቆንስላው ሄዳ ጠበቀችው ጀማል ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images
በጉዳዩ ላይ የሳዑዲ አረቢያ ምላሽ ምን ነበር?
ለሁለት ሳምንታት ያክል ሳዑዲ በጀማል እጣ ፈንታ ላይ የማውቀው ነገር የለም ስትል ቆይታ ነበር።
ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ለብሉምበርግ ሲናገሩ ''ጀማል ላይ ስለሆነው ነገር ለማወቅ ጓጉችያለሁ። ከደቂቃዎች በኋላ ወይም ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ ጉዳዩን ጨርሶ ወጥቷል'' ብለው ነበር።
''ምንም የምንደብቀው ነገር የለም'' ሲሉም ተደምጠዋል።
ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ የሳዑዲ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛው በቆንስላው ውስጥ በተፈጠረ ጸብ ምክንያት ለሞት ተዳርጓል ሲል ዘገበ።
ብሔራዊ የቴሌቪዝን ጣቢያው ጨምሮ እንደዘገበው ከጀማል ግድያ ጋር በተያያዘ 18 የሳዑዲ ዜጎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ቱርክ ጀማል ላይ ምን ደረሰ አለች?
የቱርክ ባለስልጣናት ጀማል በሳዑዲ የጸጥታ ኃይሎች በቆንጽላ ውስጥ እንዲሰቃይ ተደርጎ ተገድሏል፤ ከዚያም አስክሬኑ በሰዋራ ስፍራ ተጥሏል ይላሉ።
ቱርኮች ይህን የሚያረጋግጥ የቪዲዮ እና የድምጽ ማስረጃ አለን ይላሉ።
ይሁን እንጂ የቪዲዮ እና የድምጽ መረጃዎቹ ለህዝብ ይፋ አልሆኑም።
ሳብሃ የተሰኘ የቱርክ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በቆንጽላው ውስጥ የሚሰሩ የቱርክ ዜግነት ያላቸው ሰራተኞች በጀማል ቀጠሮ ዕለት በፍጥነት ቆንጽላውን ጥለው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር።
በጀማል ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉት የሳዑዲ የጸጥታ ኃይል አባላት እነማን ናቸው?
የቱርክ መገናኛ ብዙሃን 15 አባላት ያሉት የሳዑዲ ቡድን የጀማል ደብዛ የጠፋ ዕለት ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ኢስታንቡል ቱርክ በግል አውሮፕላን መጥተዋል።
ከ15 ሰዎች መካከል ማህር ሙትሬብ የተባለው ግለሰብ ሎንዶን በሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ የጸጥታ እና ደህንነት አባል መሆኑን ቢቢሲ አረጋግጧል።
አራት ግለሰቦች ደግሞ ከልዑል አልጋ ወራሹ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ጋር ቅርርብ አላቸው።
የቱርክ መገናኛ ብዙሃን እንደሚሉት ከሆነ 15ቱ ግለሰቦች አጥንት መቁረጫ መጋዝ ይዘው ነው የመጡት።
ከግለሰቦቹም መካከል አንዱ የሬሳ ምርመራ ባለሙያ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ይዘውት የወጡት ቪዲዮ እንደሚያሳየው ከጀማል የቀጠሮ ሰዓት አንድ ሰዓት ቀድም ብሎ የቡድኑ አባላት መኪና እያሽከረከሩ ወደ ቆንስላው ሲያመሩ ያሳያል።
ከዚያም የቡድን አባላቱ ለሁለት ተከፍለው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተመልሰው ሄደዋል።
ምረመራው እንዴት እየሄደ ነው?
ጀማል ከተሰወረ ከ13 ቀናት በኋላ የቱርክ መርማሪዎች ወደ ቆንስላው እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው ነበር።
የመርማሪ ቡድን አባላቱ ወደ ቆንስላው ከመግባታቸው በፊት የሳዑዲ ባለስልጣናት እና የጽዳት ሰራተኞች ቀድመው ገብተው ነበር።
በቆንጽላው አቅራቢያ በሚገኙ ወንዞችና ጫካዎች አቅራቢያ ምረመራዎች ተደርገዋል። ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ወደነዚህ ስፍራዎች ከቆንጽላው የተነሱ መኪኖች ሲያቀኑ ታይተዋል።
''ጀማል ተገድሏል''
ዛሬ ጠዋት ሳዑዲ ጀማል ስለመገደሉ አምናለች።
የሳዑዲ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አደል አል-ጁቤር ለፎክስ ኒውስ ሲናገሩ ''ከፍተኛ ስህተት ተፈጽሟል'' ካሉ በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ የልዑል አልጋ ወራሹ እጅ እንደሌለበት ተናግረዋል።
የተፈጸመውን ሁሉ ለማጣራት ቁርጠኛ ነን። በጉደዩ ላይ የተሳተፉትን ሁሉ እንቀጣለን'' ሲሉ ተደምጠዋል።
















