የአውሮፓ አገራት የተገደለው የሳዑዲ ጋዜጠኛ ምርመራ እንዲቀጥል አሳሰቡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
እንግሊዝ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ በቅርቡ ደብዛው የጠፋውን ታዋቂውን የሳዑዲ ጋዜጠኛ ጀማል ካሹጊን አስመልክቶ ጠበቅ ያለ ምርመራ እንፈልጋለን አሉ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው መልዕክቱን ያስተላለፉት አገራቱ ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ካለም ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባና ከሳዑዲ ባለስልጣናትም ዘርዘር ያለ መልስ እንፈልጋለን ብለዋል።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ጄሬሚ ሀንት እንዳሉት ለተፈጠረው ነገር በሙሉ የሳዑዲ አረብያ ኃላፊነት መሆኑንም አስረድተዋል።
ሳዑዲ በበኩሏ ጀማል ካሹጊ ቱርክ፣ ኢስታንቡል በሚገኘው ቆንሱላቸው ውስጥ መገደሉን ክደዋል።
የሳዑዲ የሀገሪቱ ሚዲያ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ሀገሪቷ ማንኛውንም አይነት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማስፈራሪያዎችን በፍፁም እንደማትቀበልና በግዛቷ ላይ ለሚፈፀሙ ማንኛውም ድርጊቶች ምላሹ የከፋና ፈጣን ነው ብለዋል።
ነገር ግን በትናንትናው ዕለት ንጉስ ሳልማን አቋማቸውን አለሳልሰው የቱርኩን ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋንን ሁለቱን መንግሥታት ያጣመረ የምርመራ ቡድን ማቋቋማቸውን አመስግነዋል።
ጨምረውም ከቱርክ ጋር ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት ምንም እንዳያበላሸው ገልፀዋል።
የሳዑዲ መንግሥት የሰላ ተቺ የሆነው ጋዜጠኛው ጀማል ካሹጊ ኢስታንቡል ቆንሱላ ግቢ ውስጥ ከገባ በኋላ ደብዛው ከጠፋ አስር ቀናት አልፈውታል።
የቱርክ ባለስልጣናት በበኩላቸው ጀማል ካሹጊ በቆንሱላው ውስጥ በሳዑዲ ወኪሎች እንደተገደለ የተናገሩ ሲሆን ሳዑዲ "ውሸት" በማለት ክዳዋለች።
ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ጀማል በቆንሱላው ጋብቻን በተመለከተ የሚያስጨርሰው ጉዳይ ስለነበረው ቦታው ላይ እንደተገኘ ተጠቅሷል።
የቱርክ የፀጥታ ኃይሎች ለበቢሲ እንደተናገሩት ለዋሽንግተን ፖስት ይፅፍ የነበረው ጀማል ካሹጊ በቆንሱላው ውስጥ እንደተገደለ የድምፅና የቪዲዮ ማስረጃ እንዳላቸው ነው።
ከቱርክ በኩል የተኙ ምንጮች እንዳስረዱት ጀማል 15 በሚሆኑ የሳዑዲ ወኪሎች እንደተገደለ ነው።
ከአውሮፓ አገራት በተጨማሪ ዶናልድ ትራምፕ የጀማል ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ገልፀው ሳዑዲ አጥጋቢ መልስ ልትሰጥ እንደሚገባም መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ትራምፕ ጨምረውም ጀማል ካሹጊ ቆንሱላው ውስጥ ተገድሎ ከሆነ ሳዑዲ የከፋ ቅጣት እንደሚጠብቃትም አስጠንቅቀዋል።












