"የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው ዲፕሎማሲ ቀለም አልባ ነው" የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዜጋ ተኮር እና ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ሰጥቼ እየሰራሁ ነው አለ።

ሚኒስትሩ ዛሬ ሐሙስ ማለዳ በሰጠው መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫው የኢፌድሪ መንግስት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት ላይ የማይተካ ሚና አላት ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከኤርትራው አቻቸው ኦስማን ሳለህ ወደሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ያደረጉት ከጥቂት ቀናት ጉብኝት የጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ አንድ ማሳያ ነው ያሉት የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ናቸው።

ሚኒስትር ወርቅነህ በሶማሊያ ጉብኝታቸው ወቅት የአፍሪቃ ቀንድ ሰላም እና ደህንነት እውን እንዲሆን እንዲሁም ለቀጠናው ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር በጋራ ለመስራት ከኤርትራ እና ሶማሊያ አቻዎቻቸው ጋር መወያየታቸውን ይህንንም የሚያስረግጥ የጋራ መግለጫ መስጣታቸውን አቶ መለስ አክለው ተናግረዋል።

በሶስቱ አገራት መካከል በኤርትራ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል። "ጎረቤትን የሚያስቀድም ዲፕሎማሲ፣ የጎረቤቶቻችን እጣ ፈንታ ከእኛ ጋር የተሳሰረ ነው በሚል ፅኑ እምነት ላይ የተመሠረተ ነው" ብለዋል አቶ መለስ።

የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለውን ዲፕሎማሲ "ቀለም አልባ ነው" ሲሉም ገልፀውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በፈረንሳይ እና በጀርመን በሚያደርጓቸው ጉብኝቶች በአፍሪካ ቀንድ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።

ጥቅምት 21 ቀን"አንድ ሆነን እንነሳ፤ ወደፊቱን እንገንባ" በሚል መሪ ቃል በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ቀን ይከበራል።

በዕለቱም በአውሮፓ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በጀርመኗ ፍራንክፈርት ይሰበሰባሉ ተብሏል።

እንደአቶ መለስ ገለፃ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ወይዘሮ ብርቱካን አያኖ የሚመራ እና በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች የተካተቱበት ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል።

"ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የማይሳተፉበት የአገር ግንባታ ሒደት ስኬታማ አይሆንም" ሲሉ አቶ መለስ የዕለቱን አስፈላጊነት አብራርተዋል።

"በቀድሞ በሬ በማረስ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፤ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል። እነርሱም የአገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር ተገናኝተው፤ እየተካሄድ ስላለው ለውጥ ያስረዳሉ፤ ኢትዮጵያዊያኑ ሊኖራቸው የሚችለውን አስተዋፅዖ ይገልፃሉ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያዊያኑን ራዕይ እና ፍላጎት ያዳምጣሉ እንደቃል አቀባዩ ገለፃ።

አውሮፓ ውስጥ በሚገኙ 13 ሚሲዮኖች እና የቆንስላ ፅህፈት ቤቶች ዝግጅቶች እየተከናወኑ ሲሆን ከ20 ሺህ እስከ 25 ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ዝርያ ያላቸው ዜጎች ይገኛሉ ተብሎም ይጠበቃል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የመዋቅር ማሻሻያ እያደረገ ነው፤ ይህም በሚሲዮኖች እንዲሁም በዋናው መስሪያ ቤት ውስጥ ይከናወናል ብለዋል አቶ መለስ። "ይሄንን ተቋም የሃያ አንደኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን ማድረግ ያስፈጋል፤ እንደዚያ ዓይነት ተቋም ለመፍጠር የሚያስችል የማሻሻያ ሥራ እየተካሄደ ነው።"